የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከቀይ ባህር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ጋር በተጣጣመ መልኩ ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል-ጥናት

69
አዲስ አበባ ነሀሴ 18/2010 የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአሁኑ ወቅት በቀይ ባህር ካለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ጋር በተጣጣመ መልኩ መሻሻል እንደሚገባ አንድ ጥናት አመለከተ። የቅደስት ማርያም ዩኒቨርስቲ 10ኛውን ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት አካሄዷል። የቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ የምርምር አማካሪ አቶ አሉላ ኔራ ባቀረቡት ጥናት እንዳመለከቱት በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለው የአገሪቷ  የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከ15 ዓመታት በላይ የቆየ ስለሆነ በቀይ ባህር ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባገናዘበ መልኩ መሻሻል አለበት። የፖሊሲው ውጤታማነት ተገምግሞ ያስገኙት ውጤቶቹ ይፋ እንዳልተደረጉም ጥናቱ አመልክቷል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለቀጣናው ሰላም ያስገኛቸው አንጻራዊ ውጤቶችና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ምላሽ የመስጠት ብቃት፣ በቀይ ባህር አካባቢ ወታደራዊ ይዞታ ያላቸው የኤርትራ፣ የየመንና የግብጽ ሁኔታዎችን ጥናቱ ትኩረት ያደረገባቸው ነጥቦች ናቸው። በቀጣናው አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ከማድረጉም በላይ፣ ከግብጽና ከኤርትራ በስተቀር ኢኮኖሚያዊ ትብብር መፍጠር፣ በተለይም በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ፖሊሲው ባለፉት ዓመታት ያስገኛቸው ውጤቶች እንደሆኑም ጥናቱ አመልክቷል። በአሁኑ ወቅት በቀይ ባህር ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ፣ ኤርትራ ባላት መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ተፈላጊነቷ በመጨመሩና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ፖሊሲውን ማሻሻል እንደሚያስፈልግም ጥናቱ ጠቁሟል። ግብጽ በቀይ ባህር ላይ ካላት ይዞታና በመካከለኛው ምስራቅ ካላት ተፅዕኖ ፈጣሪነት አኳያ በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የመፍጠር ዕድሏ ሰፊ በመሆኑ ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣመ ፖሊሲ  ማውጣት አስፈላጊ እንደሆነም አመልክቷል። እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የመን ከምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታና ለኤርትራ ካላት ቅርበት አንጻር የኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል በጥናቱ ተመልክቷል። በአጠቃላይ ጥናቱ ኤርትራ፣የመንና ግብጽ በባህረ ሰላጤው ላይ የኢትዮጵያ ዕድገትና ደህንነትና ዲሞክራሲያዊ ግንባታ ስርዓት ላይ ተጽዕኖ የመፍጠር ዕድላቸው እየጨመረ መምጣቱን ጠቁሟል። በኢትዮጵያ ላይ የሚኖራቸው ተጽዕኖ ከ15 አመታት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር የተለየ መሆኑንም ገልጸዋል። በመሆኑም የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በተለይም ከየመን ፣ኤርትራና ግብጽ ካሉበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ጥናቱ እንደሚያመለክት አቶ አሉላ ተናግረዋል  ። ሁሉን አቀፍ የሆነና ቀይ ባህር ላይ ያተኮረ የፖሊሲ ማሻሻያም አስፈላጊ ነው ያሉት። የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር አየነው ብርሃኑ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የፌዴራላዊ ስርዓትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና በተመለከተ ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያሉባቸው ክፍተቶች እንዲሁም የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ለመገንባት መሰራት ያለባቸው ስራዎች ላይ ጥናት አቅርበዋል። በገዥው ፓርቲ በኩል ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታ ያለመፍጠር፣ የፍትህ አካላትና የምርጫ ቦርድ የመሳሰሉት  ለገዥው ፓርቲ ማድላት፣ እንዲሁም ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ከመገንባት አንጻር ያሉትን ክፍተቶች አንስተዋል። ብሄር ተኮር አድርጎ መስራት፣ አማራጭ የፖሊሲ ሀሳቦችን ይዞ አለመቅረብ፣ በበቂ አቅም ያለመደራጀት ክፍተቶችን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ችግሮች መካከልም ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለውን ለውጥ በመጠቀም ለአገሪቱ ዕድገት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል። በቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የዕውቀት ማኔጅመንት ዳይሬክተር ዶክተር ከበደ ካሳ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ማካሄድ፣ የዕውቀት ሽግግር መፍጠር፣ የተሰሩ ምርምሮችን ለህትመት ማብቃትና ለባለ ድርሻ አካላት ማሰራጨት በየዘርፉ ሰፊ ጥናት እንዲካሄድ ማነሳሳት የሴሚናሩ ዓላማዎች ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም