አሸባሪው የህወሃት ቡድን በኮምቦልቻ ከተማ በአምስት ፋብሪካዎች ብቻ ከሩብ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት አድርሷል

211

ታህሳስ 5/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በኮምቦልቻ ከተማ በአምስት ፋብሪካዎች ላይ ብቻ ከሩብ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ዘረፋና ወድመት ፈፅሟል፡፡

በከተማዋ ከ30 በላይ የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች የአሸባሪ ቡድኑ እኩይ እጆች አርፈውባቸዋል።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተመራ የጋዜጠኞች ቡድን የደረሰውን ጉዳት ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

አሸባሪ ቡድኑ ኢንዱስትሪዎችን የሚዘርፍ በዘርፉ የሰለጠነ ኃይል አሰማርቶ የእያንዳንዱን ፋብሪካ ቀልፍ መሳሪያዎች፤ ለአብነትም ሞተሮች፣ኮምፒውተራይዝድ ማሽኖች እና በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገቡ መለዋወጫዎችን ዘርፏል።

በተመሳሳይ በሁሉም ፋብሪካዎች ያሉ የአስተዳደር ቢሮዎችን ሙሉ በሙሉ ማውደሙንና በቀላሉ የማይተኩ ሰነዶችን ደግሞ ከጥቅም ውጭ ማድረጉን የኢዜአ ሪፖርተር ታዝቧል።

ከ4 ሺህ በላይ ሰራተኞች ባቀፈው የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ በወጪ ምርቶችን ላይ በሚሰሩ ስድስት የውጭ ኩባንያዎች ላይ ያለቀላቸው ምርቶች እና የምርት ግብዓቶች፣ የማሽነሪ ክፍሎች እንዲሁም በፓርኩ አስተዳደር ንብረቶች ላይ ዘረፋና የሰነድ ውድመት አድርሷል።

በተጨማሪ በጥረት ኮርፖሬት ስር ያሉ የኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ እና ዋልያ ቆርኬ ፋብሪካ ላይም ጉዳት ደርሷል።

ከ1 ሺህ 500 በላይ ሰራተኞች ያሉትና በዓመት ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚያስገኘው አንጋፋው የኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን ባይገለፅም፤ ያለቀላቸው ምርቶች፣ የአስተዳደር ክፍሎች እና የሰራተኞች መገልገያ ንብረቶች ተዘርፈዋል፤ ሰነዶችም ከጥቅም ውጭ ሆነዋል።

በራሱ ጥሬ ዕቃ ቆርኬ አምርቶ ለገበያ የሚያቀርበውና በኢትዮጵያ ብቸኛው የቆሮኬ ፋብሪካ በሆነው “ዋልያ ኮርኬ” ከ18 እስከ 20 ሚሊዮን ብር ውድመት እንደተፈፀመበትም ተገልጿል።

በ2006 ዓ.ም ወደ ስራ የገባውና ለ240 ዜጎች የስራ እድል የፈጠረው “ሁዋክሱ” የተሰኘው የቻይና የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ላይም በምርት፣ በግብዓት እና በማሽኖች ላይ ዘረፋ ተፈፅሟል።

በኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ ውስጥ በ13 ኮንቴነሮች የተጫነ ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሃብት ተዘርፏል፤ በተጨማሪም ደረቅ ወደቡ ስራ በማቆሙ ምክንያት እስካሁን 60 ሚሊዮን ብር ትርፍ አጥቷል።

ከ300 በላይ ሰራተኞችን የያዘው “ኢትውድ ማኑፋክቸሪንግ” የተሰኘው የቻይና የእንጨት ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካም በተመሳሳይ በአሸባሪ ቡድኑ ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት ተፈፅሞበታል።

አሸባሪ ቡድኑ ሒፋም/ሰይድ አሊ የማዳበሪያ ከረጢት ፋብሪካ እና አማር የከረጢት ፋብሪካዎች ላይ ቁልፍ የማሽን አካል ክፍሎች፣ በምርቶች፣ በመለዋወጫዎች እና በተንቀሳቃሽ ንብረቶች ላይ ዘረፋ ፈጽሟል፤ መውሰድ የማይችለውን ደግሞ አውድሟል፡፡

በዚህም ከ300 በላይ ሰራተኞች የስራ ዕድል የፈጠረው በሒፋም/ሰይድ አሊ ከረጢት ፋብሪካ በአጠቃላይ 80 ሚሊዮን፤ ከ500 በላይ ሰራተኞችን በሚያስተዳድረው አማር ከረጢት ፋብሪካ ደግሞ ከ40 ሚሊየን ብር በላይ ዘረፋ ተፈፅሞባቸዋል።

በተመሳሳይ አሸባሪ ቡድኑ በከተማዋ በሚገኝ አንድ የአልኮል ፋብሪካ ላይ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ዘረፋና ውድመት ፈጽሟል፡፡

በአጠቃላይ በተለያዩ ምርቶች ላይ በተሰማሩ አምስት ፋብሪካዎች ብቻ ማለትም በሁዋክሱ ጨርቃጨርቅ፣ በአማር ከረጢት ፋብሪካ፣ በሒፋም/ሰይድ አሊ ከረጢት ፋብሪካ፣ በዋልያ ቆርኬ ማምረቻ እና በአንድ የአልኮል ፋብሪካ ከሩብ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ዘረፋና ውድመት መፈጸሙ ነው የተገለጸው።

የኢንደስትሪ ሚኒስቴር እና የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ጉዳት የደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ ለማስገባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከባለሃብቶች ጋር በዛሬው ዕለት ምክክር አድርገዋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው ባለሃብቶችም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ካደረጉላቸው በአጠረ ጊዜ ውስጥ የወደሙ የማሽን ንብረቶች በመተካት ወደ ስራ ለመመለስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።