ሀገርን ለማዳን በጋራ እንደዘመትነው ሁሉ የሴቶችን ጥቃት ለማስቆም በአንድነት መቆም ይኖርብናል

80

ጭሮ፤ ታህሳስ 5/2014/ኢዜአ/ ሀገርን ለማዳን በጋራ እንደዘመትነው ሁሉ የሴቶችን ጥቃት ለማስቆም በአንድነት መቆም ይኖርብናል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሰሚራ ፋሪስ ተናገሩ።

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ከክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር የሴቶችን ጥቃት መከላከል በሚቻልበት ዙሪያ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በጭሮ ከተማ ተካሄዷል።

የቢሮው ምክትል  ኃላፊ  በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት አሸባሪው ህወሀትና ሸኔ በሀገር ላይ ከሚያደርሱት አደጋ የሚተናነስ አይደለም።

ሀገሪቱን ከአሸባሪው የህወሃት ቡድን የጥፋት ተልዕኮ  ለመከላከል በጋራ እንደዘመትነው ሁሉ የሴቶችን ጥቃት ለማስቆም በአንድነት መቆም ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡

ሴቶች በውሳኔ ሰጪነት ሃላፊነት ተሰጥቷቸው ውጤታማነታቸው በተግባር እየተረጋገጠ መሆኑን ያስታወሱት  ወይዘሮ ሰሚራ፤ የሚደርስባቸውን ጥቃት በመከላከል ይህንን አቅማቸውን መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል።

በተለይ የህግ፣ የትምህርትና የጤና ሴክተሮች በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ማንኛውንም ጥቃት ለመከላከል ብሎም ለማስቆም ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የምዕራብ ሐረርጌ ዞን   ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ  ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አስሊያ የሱፍ በበኩላቸው፤ በፆታዊ ጥቃት ምክንያት  በሴቶች ላይ የሚደርሰውን  ጉዳት ለመከላከል   በጋራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ዞኑ  በሴት ልጆች ላይ የሚደርሱ ያለ እድሜ ጋብቻ፣ የሴት ልጅ ግርዛት  ፣ፆታዊም ሆነ ማናቸውም ጥቃት ለማስቆም እንዲያግዝ በቅርቡ በየደረጃው የማህበረሰብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ መካሄዱን ገልጸዋል፡፡

ይህንን አጠናክሮ በማስቀጠል ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት  ከህግ አካላትና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር በመቀናጀት መሰራት እንደሚገባ  ጠቁመዋል፡፡

በጭሮ አጠቃላይ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ዶክተር  ሙሉጌታ ጥሩነህ እንዳሉት፤  በሴቶችና ህፃናት ላይ እየደረሰ ባለው ፆታዊ ጥቃት ምክንያት ለአእምሯዊና አካላዊ ጉዳት እንዲሁም ለህልፈት የሚዳረጉ ብዙዎች  ናቸው።

ይህንን ችግር ለመፍታትና ሴቶች ላይ የሚደርሱትን የትኞቹንም ጥቃቶች መከላከል የሁሉም የዕለት ተዕለት ተግባር መሆን አለበት ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም