በኢትዮጵያ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቋቋም እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል

218

ታህሳስ 5 ቀን 2014 (ኢዜአ) በወራሪው የጠላት ሃይል ላይ መንግስት እየወሰደ ካለው የተጠናከረ የማጥቃት እርምጃ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቋቋም እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ በአደጋ ምላሽ አሰጣጥ እና መልሶ ማቋቋም ተልዕኮ ዙሪያ ለመንግስት አስፈፃሚ አካላት ግልፅ የስራ ስምሪት የሰጠበት መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የብሄራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአሁን ጊዜ መንግስት በወራሪ የጠላት ሃይል ላይ እየወሰደ የሚገኘው የማጥቃት እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በወራሪ የህወሓት ሀይል ላይ ከሚወሰደው የማጥቃት እርምጃ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ የሚደርሱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ለመቋቋም እና ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን ሁለንተናዊ ጥረት በቅንጅት ለመምራት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁንም አቶ ደመቀ ይፋ አድርገዋል።

በጠላት ወረራ ተይዘው የተለቀቁ ፤ ለጊዜው በጠላት እጅ ባሉ አካባቢዎች እንዲሁም በአርብቶ አደር አካባቢዎች የደረሰውን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም የሚያስችሉ ሁሉአቀፍ ድጋፎች በልዩ ትኩረት ይከናወናሉ ሲሉ ነው የገለጹት።

የተቋቋመው ግብረ ሀይል “በዚህ ረገድ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት የዕለት ደራሽ ዕርዳታ አቅርቦት፣ የማገገም እና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን አስመልክቶ በተጠና እና በተጠናከረ ቅንጅት ኃላፊነታቸውን በጋራ ሊወጡ ይገባል” ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ለተከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በሚሰጡ ምላሾችና የመልሶ ማቋቋም ተግባራት ዙሪያ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት በጋራ ሊረባረቡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት በጠላት ላይ በሚደረገው መጠነ ሰፊ የማጥቃት ዘመቻን ተከትሎ ነፃ የሚወጡ አካባቢዎችን መሰረታዊ አገልግሎቶች ማስጀመር የሚያስችሉ ድጋፎችን በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ ፤ እያንዳንዱ ሴክተር መስሪያ ቤት ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቅ እንዳለበትም አስምረውበታል።

በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ ካላት መልክዓ -ምድራዊ አቀማመጥ እና የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ሁኔታዎች በተያያዘ ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተጋላጭ እንደሆነች አቶ ደመቀ አብራርተዋል።

በመሆኑም በገጠር አርሶ አደሩ ፈጥኖ ወደ በጋ የግብርና ሥራ እንዲገባ የመስኖ አለኝታ ባለባቸው አካባቢዎች የተለያዩ አስፈላጊ የእርሻ ግብዓቶችን የማቅረብ ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

በተለያየ አግባብ በተደራጁ የድጋፍ ሰጪ እና የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴዎች በመካከላቸው ያለውን የስራ ድግግሞሽ በማስቀረት ተጠያቂነትንና ኃላፊነትን በሚያረጋግጥ መንገድ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት አቶ ደመቀ።

ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ በአደጋ ምላሽ አሰጣጥ እና መልሶ ማቋቋም ተልዕኮ ዙሪያ ለመንግስት አስፈፃሚ አካላት ግልፅ የስራ ስምሪት መስጠቱን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

-አካባቢህን ጠብቅ፣ _

ወደ ግንባር ዝመት፣_

መከላከያን ደግፍ።