ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጀርመን መንግስት የልኡካን ቡድንን አነጋገሩ

84
አዲስ አበባ ነሃሴ 18/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጀርመን የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስትር ገርድ ሙለር የተመራውን የሀገሪቱ መንግስት የልዑካን ቡድን ዛሬ በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ። የጠቅላይ ሚኒስትሩና የጀርመን መንግስት ልዑካን ቡድን ውይይት ትኩረትም የሁለትዮሽ ግንኙነትና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጉዳዮች እንደነበር ውይይቱን የተከታተሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ ለኢዜአ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ፣ ከኤርትራ ጋር የነበረው የቆየ አለመግባባት የተፈታበትን መንገድ ጨምሮ በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድን አካባቢ ሰላም ለማምጣት እየተደረገ ያለውን ጥረት አስመልክተው ለልዑኩ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የጀርመን መንግስት ለኢትዮጵያ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ በተለይም በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ እንደዚሁም በግብርና ልማት የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል። የጀርመኑ የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ሚኒስትር በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እየተፈጠረ ያለውን የሰላምና መረጋጋት ሁኔታ አድንቀዋል። በተለይም የኢትዮጵያ መንግስት በወሰዳቸው የለውጥ አርምጃዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጣው ውጤት የሚያስደንቅ መሆኑን ሚኒስትሩ መናገራቸውን አቶ ፍፁም ጠቅሰዋል። በአካባቢው በአሁኑ ወቅት የሚታየው ለውጥ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም