የጎንደር ከተማ በ'አንድ ሚሊዮን ወደ ሀገር ቤት' ጥሪ መሰረት የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅት ጀምሯል

97

ጎንደር፣ ታህሳስ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ 'አንድ ሚሊዮን ወደ ሀገር ቤት' ጥሪ መሰረት የሚመጡ የዳያስፖራ እንግዶችን ለማስተናገድ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ዝግጅት ጀምሯል።

የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለዳያስፖራው የቀረበው የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ የሚያነቃቃ ነው።

በተለይም ጥንታዊና ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ በታላቅ ድምቀት ለምታስተናግደው የጥምቀት በዓል መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።ለዳያስፖራው የቀረበው ጥሪ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና አሸባሪው ህወሃት በፈጸመው ሳቢያ ተቀዛቅዞ የነበረውን ቱሪዝምና ኢንቨሰትመንት ፍሰት እንደሚያነቃቃው የገለጹት አቶ ዘውዱ፤ ጥሪው ለከተማዋ ምቹ እድል መፍጠሩን አመልክተዋል።

የከተማው አስተዳደር ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለኢንቨስትመንት የሚውል መሬት ከሶስተኛ ወገን ነጻ አድርጎ በማዘጋጀት ከወዲሁ እየጠበቀ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የዘንድሮን የጥምቀት በዓል በድምቀት ለማክበር የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ከወዲሁ ዝግጅት መጀመሩን የጠቀሱት የከተማው ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ቻላቸው ዳኘ፤ በዓሉ በጎንደር ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መንገድ በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት እንደሚከበር አስታውሰዋል።

"በዓለም በማይዳሰሱ ቅርሶች መመዝገቡ ደግሞ የውጭ ቱሪስቶችን ቀልብ ለመሳብ አስችሎታል" ብለዋል፡፡

ከበዓሉ ቀደም ብሎም የቱሪዝም ፍሰቱን ለመጨመር ያለመና የአካባቢውን ባህል፣ ወግና እምነት እንዲሁም ትውፊቶች የሚያስተዋውቅ የባህል ፌስቲቫል እንደሚካሄድ ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

በበአሉ ለሚታደሙ የሀይማኖቱ ተከታዮችና መሪዎች እንዲሁም ለእንግዶች ማረፊያ እየተመቻቸ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም