የኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በቅርቡ ወደስራ ይመለሳል

273

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሃት ወራሪ ኃይሎች በካምፕነት የተጠቀሙበትና ያወደሙት የኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በቅርቡ ወደስራ እንደሚመለስ የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ ጀማል ተናገሩ፡፡

ፋብሪካው  ከ1 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠሩን ስራ አስኪያጁ አስታውሰዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ የፋብሪካውን ምርቶችና መገልገያ ቁሳቁሶች ከመዝረፍ ባሻገር በካምፕነት ሲጠቀምበት መቆየቱንም ነው የተናገሩት፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በፋብሪካው ግቢ ውስጥ ምሽግ መስራቱን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ፋብሪካው አስፈላጊውን ጥገና ተደርጎለት በቅርብ ቀን ወደ ስራ እንደሚመለስም ተናግረዋል።

40 ዓመታት ዕድሜ ያስቆጠረው ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በዓመት 10 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ያስገኝ እንደነበር ስራ አስኪያጁ አቶ ሙስጠፋ ጀማል አስረድተዋል።

በተያያዘ ዜና የጥረት እህት ኩባንያ የሆነው ዋልያ ቆርኪ ፋብሪካ ከ18 እስከ 20 ሚሊየን ብር የሚገመት ሃብት ውድመትና ዘረፋ እንደደረሰበት የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ሰማዓየሁ ገልፀዋል።

ፋብሪካው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ተሟልተውለት በሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደስራ ለማስገባት መታቀዱንም ነው የተናገሩት፡፡