ጠንካራና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት አፍሪካዊ የመሪነት እሴትና አቅምን ማጎልበት ይገባል

76

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) ጠንካራና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት አፍሪካዊ የመሪነት እሴትና አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዶክተር ምህረት ደበበ ተናገሩ።

የአፍሪካ የፀረ-ቅኝ ግዛት ንቅናቄ /ፓን አፍሪካኒዝም/ የጥቁሮችን የመብት አቀንቃኝነት፣ የጋራ ትብብርና ፖለቲካዊ ቁርኝት እንዲሁም የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን ያጠቃልላል።

በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ እስከ አሁንም በትግሉ ቀጥላበታለች።

በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ አገዛዝ ነፃ እንዲወጡ አስተዋፅኦ የነበራት ኢትዮጵያ ዛሬም የአፍሪካ ችግር በአፍሪካዊያን ይፈታ የሚል አቋሟን ታራምዳለች።

'አፍሪካዊያን ችግሮቻቸውን ማስወገድ የሚችሉት መከፋፈልና መለያየትን አጥብበው አንድነት ሲፈጥሩ ብቻ ነው' የምትለው ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ዛሬም አፍሪካዊያንን በ"በቃ" እንቅስቃሴ ማስተሳሰር ችላለች።

የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዶክተር ምህረት ደበበ፤ ጠንካራና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት አፍሪካዊ የመሪነት እሴትና አቅምን ማጎልበት ይገባል ይላሉ።

አፍሪካ ተወዳዳሪነቷ አድጎ በቂ ተፅዕኖ መፍጠር የምትችልበትን ዕድል መፍጠር እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ።

አፍሪካ በቂ ሃብትና የሰው ኃይል እንዳላት የጠቀሱት ዶክተር ምሕረት እምቅ ሃብቷን በአግባቡ ለመጠቀም የአህጉሪቷ የትብብር ልማት አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳሉ።

ለዚህ ደግሞ አፍሪካ በራሷ ሃብትና የሰው ኃይል ተጠቅማ ከዓለም ኃያላን አገራት እኩል እንድትቆም የተጀመሩ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

አፍሪካ ከምዕራባዊያን ጥገኝነትና ጫና እንድትላቀቅና ነፃ የሆነ አህጉራዊ ርዕዮተ ዓለምና የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንድትከተል አፍሪካዊ የመሪነት እሴት አቅምን ይበልጥ ማጎልበት ያስፈልጋልም ብለዋል።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ደግሞ የአፍሪካዊያን የምርምርና የሐሳብ ማንሸራሸሪያ በመሆን እንደሚያገለግል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

አፍሪካ ወደፊት የምትሄደው "አፍሪካ ደሃ አይደለችም የበለፀገች ናት፤ አፍሪካ ወጣት ናት አላረጀችም፤ አፍሪካ ብርሃናማ ነች ጨለማ አህጉር አይደለችም" የሚሉት ሃሳቦች በመሪዎቿ ሲሰርጹ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም