በዘመቻው ምክንያት የከፋ የኢኮኖሚ ጫና እንዳይፈጠር በቴክኖሎጂ የታገዘ ድጋፍ እናደርጋለን

266

ታህሳስ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) በህብረ ብሔራዊ አንድነት ዘመቻው ምክንያት የከፋ የኢኮኖሚ ጫና እንዳይፈጠር በቴክኖሎጂ የታገዘ ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት አመራሮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አመራሮች በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ ስራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ እና  የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ እንደሚሉት፤  ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት የሙያ መስክ ጠንክሮ በመስራት ለአገሩ ህልውና ሚናውን መወጣት አለበት፡፡

ዜጎች በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ለተሰለፉት የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት እያደረጉት ያለውን የደጀንነት ተግባርም አድንቀዋል፡፡

ለሰራዊቱ ከሚደረገው ድጋፍ ጎን ለጎን ሁሉም በተሰማራበት የስራ መስክ ጠንክሮ በመስራት የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዳይቀዛቀዝ የሚችለውን ሁሉ ማድረግ አለበት ነው ያሉት።

በመሆኑም በህልውና ጦርነቱ ምክንያት በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለመቋቋም በተማሩበት የቴክኖሎጂ ዘርፍ አስፈላውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ሁሉም ተባብሮ ከሰራ በኢኮኖሚው መስክ ድል መጎናጸፍ እንደሚቻልም የኢንስቲትዩቶቹ ሃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግንባታ ቀጣይነት እንዲኖረው የባዮ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ጥቅም ላይ ማዋል ብዙ ዋጋ እንዳለው ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ አንስተዋል።

በዚህም የግብርና፣ የጤናና የኢንዱስትሪ ዘርፎችን መለወጥ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ አብዲሳ በበኩላቸው የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተልዕኮውን ለማስፈጸም በተለየ ዝግጁነት ስራዎችን እጠተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።