የህልውና ዘመቻው ኢትዮጵያዊነት ተጠናክሮ መቀጠሉን አሳይቷል

206

ባህር ዳር፣ ታህሳስ 4/2014 ( ኢዜአ) ”የህልውና ዘመቻው ኢትዮጵያዊነት ተጠናክሮ መቀጠሉን አሳይቷል” ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስታወቁ።

ከአማራ ክልል ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች በአገራዊና ክልላዊ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ የመከሩበት  መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።


የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በመድረኩ ላይ እንዳሉት የአሸባሪው የህወሃት ቡድን ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ንፁሃን ዜጎችን በግፍ ገድሏል፤ የህዝብ ሃብትና ንብረትንም  አውድሟል።

አሸባሪው ህወሀት ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበርና በስልጣን ዘመኑ  በዘረፈው  የሀገር ሀብት በመታገዝ ኢትዮጵያን አፍርሶ ታላቋን ትግራይ መገንባትን አላማ አድርጎ መነሳቱን ተናግረዋል ።

ቡድኑ አላማ አድርጎ የተነሳውን ሀገር የማፍረስ ሴራ ለማሳካት የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ኢትዮጵያዊያን  በአንድነት መነሳታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም የአሸባሪውን ወረራ ለመመከት እየተካሄደ ያለው የህልውና ዘመቻ የኢትዮጵያዊያንን የአርበኝነት፣ የአንድነትና የወንድማማችነት መንፈስ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያሳየ መሆኑን አመልክተዋል ።

“የአሸባሪውን ኢትዮጵያን የመበተን ህልሙን ለማምከን እየተካሄደ ያለው የህልውና ጦርነት ኢትዮጵያዊነት ትስስር  መጠናከሩን ያሳየ ነው” ብለዋል  ።
 

“የውስጥና የውጭ ጠላቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን ” ያሉት አቶ ገዱ  በተለይም ወጣቱ ሀገሪቱን እያጋጠማት ካለው ስጋት ለመታደግ  ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ወጣቱ መከላከያ ሰራዊቱን በመቀላቀል የአገርን ሉአላዊነትና ዳር ድንበር በማስጠበቅ እንደ አባቶቹ ታሪክ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

ሌተናል ጀነራል ሃሰን ኢብራሂም በበኩላቸው አሸባሪው ህወሃት ህዝብን እንደ ጠላት ፈርጆ ንፁሃንን በግፍ እየገደለና እያፈናቀለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

“አሸባሪው ቡድን ካለው የህዝብ ጥላቻ በመነሳት አገር ለመበተን አልሞ የተነሳበትን ሴራ ለማምከን ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ” ብለዋል።

“የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የቡድኑን እኩይ ተግባር ለማምከን በየግምባሩ ጀብድ እየፈፀሙ ነው ” ያሉት  ሌተናል ጀነራል ሃሰን ወጣቱ የወራሪውን ጥቃት በመመከት የሀገሩን ክብርና ሉአላዊነት ለማስከበር መከላከያ ሰራዊቱን ሊቀላቀል እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።


የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት በሪሁን ተፈራ በበኩሉ ኢትዮጵያ አሸባሪው ቡድኑን  ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ጠላት ማንበርከክ የሚችል ሰራዊት ለመገንባት በምታደርገው ጉዞ ወጣቱ መሳተፍ እንዳለበት አመልክቷል።

“ወጣቱ የአገር መከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀል የማንቃትና የመመልመል ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” ሲል ጠቁሟል ።

የአገር መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል የሀገርን ዳር ድንበርና ክብር ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆኑን  ወጣት በሪሁን ገልጿል።

መከላከያ ሰራዊትን መቀላቀል የኢትዮጵያዊያን ኩራት ነው” ያለው ወጣት ሙሉቀን አዳሙ በበኩሉ መከላከያ ሰራዊትን መቀላቀል ደግሞ የሀገር ክብር መሆኑን በመረዳት  ሁሉም ዜጋ ሃላፊነቱን መወጣት እንደሚጠበቅበት አመላክቷል።