ለሀገር ህልውና መጠበቅ ድጋፋቸውን በማጎልበት የክልሉን ልማት ለማጠናከር እየተሰራ ነው

241

ጋምቤላ ፤ ታህሳስ 4/2014(ኢዜአ)ለሀገር ህልውና መጠበቅ ድጋፋቸውን በማጎልበት በክልሉ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ሦስት ወረዳዎች ከ242 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ለሚገነቡ አራት መለስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፤  አሸባሪው ህወሓትና ተላላኪዎቹ ሀገር የማፍረስ እኩይ ሴራቸውን ለመቀልበስ ክልሉ ድጋፉን ከማጎልበት ባሻገር የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው።

በክልሉ ያለውን ሰፊ የመሬትና የውሃ ሀብት አቀናጅቶ ማልማት እንደሚገባ አመልክተው፤ የመስኖን ልማት በማስፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጠንክረው እንዲሰሩም አሳስበዋል።

የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው የመስኖ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁም አመራሩና ህብረተሰቡ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።

የክልሉ እርሻ ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ በበኩላቸው፤ በተለያዩ ጊዜያት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ ቢጀመርም በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ባለመጠናቀቃቸው የታለመውን ግብ ማሳካት እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል።

ካለፉት ፕሮጀክቶች ትምህርት ወስዶ አዲሶቹን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማከናወን ህብረተሰቡ  ፕሮጀክቶቹን እንደራሱ ንብረት በማየት ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ሃላፊው እንዳሉት፤ ፕሮጀክቶቹ በምስራቅ አፍሪካ የስደተኞች ተጽዕኖ ምላሽ ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ የሚገነቡ ናቸው።

ፕሮጀክቶቹ ከ242 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥም ግንባታቸው ተጠናቆ  ለአገልግሎት ለማብቃት ነው የታቀደው።  

ተጠናቀው አገልግሎት ሲጀምሩም  262 ሄክታር በማልማት ከአንድ ሺህ በላይ  አባወራ  አርሶ አደሮችን  ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ከፕሮጀክቶቹ የሥራ ተቋራጮች መካከል አቶ ኡጀሉ አደይ እና አቶ ቢኒያም አወል በሰጡት አስተያየት የግንባታ ስራውን በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በጥራት ገንብተው ለማስረከብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ለስኬታማነቱም የአመራሩና የአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፍና ትብብር እንዳይለያቸውም አመልክተዋል።

በጋምቤላ ክልል ትልቅና አነስተኛ ወንዞችን በመጠቀም ከ780ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት የሚያስችል አቅም እንዳለ ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮው  የተገኘው መረጃ ያመለክታል።