በአሸባሪዎቹ ምክንያት የደረሰውን ችግር ለመቅረፍ አሜሪካ ከኢትዮጵያውያን ጎን በመቆም ቁርጠኛ ውሳኔ ልታሳልፍ ይገባል

169

ታህሳስ 04 2014(ኢዜአ) በአሸባሪዎቹ የመስፋፋት ፍላጎት ምክንያት የደረሰውን ችግር ለመቅረፍ አሜሪካ ከኢትዮጵያውያን ጎን በመቆም በአሸባሪዎቹ ላይ ቁርጠኛ ውሳኔ ልታሳልፍ ይገባል ሲሉ የእስራኤል የክነሴት አባልና የቀድሞ የደህንነት መስሪያ ቤት ምክትል ኃላፊ ጋዲ የቨርካን አመለከቱ።

የእስራኤል የቀድሞ የደህንነት መስሪያ ቤት ምክትል ኃላፊ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የክነሴት ምክር ቤት አባል ጋዲ የቨርካን ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በላኩት ደብዳቤ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የያዘው የተሳሰተ ፖሊሲ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ የስልጣኔ ባለቤት መሆኗን አውስተው፤ “እስራኤላውያንም በጋራ እሴት አብረው ከኖሩባቸው ወዳጅ አገር አንዷ ናት” ብለዋል።“የኢትዮጵያ ደህንነት መጠበቅና የህዝቦቿ ሰላም መሆን ቅድሚያ የምንሰጠው አጀንዳችን ነው” በማለት አመልክተው፤ በአባሸሪው ህወሃት ምክንያት በአማራና አፋር ክልሎች በዜጎች ላይ የተፈጠረው ከፍተኛ ችግር እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።

“የደረሰውን ችግር ለመቅረፍና መፍትሄ ለመስጠት ጊዜው አሁን ነው፣ የአሜሪካ መንግስት ግልጽ የሆነ መልዕክቱን ለአሸባሪዎቹ በማስተላለፍ በዜጎች ላይ የተከሰተውን ችግር መቅረፍና ጦርነቱን በማስቆም ወደ ሰላም መምጣት ያስፈልጋል” ብለዋል።

“ኢትዮጵያ ሁሉን ያማከለ ዴሞክራሲ ግንባታ ላይ ትገኛለች፣ ለዚህም ማሳየው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የተሳትፉበት ግልጽና ገለልተኛ ሆኖ የተጠናቀቀው ምርጫ ነው” ሲሉ ጠቅሰዋል።

አለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህንን እውቅና በመስጠት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የሚያከናውናቸውን ተግባራት ሊደግፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ለአሜሪካና እስራኤል አጋርና ወዳጅ ናት ሲሉ አብራርተው “የአሜሪካ መንግስት በአሸባሪዎች ፍላጎት ምክንያት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ለማስቆም በአሸባሪዎቹ ላይ ቁርጠኛ ውሳኔ በማሳለፍ ከኢትዮጵያውያን ጎን ሊቆም ይገበል” ብለዋል።

“የአሜሪካ መንግስት የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታትም ገለልተኛ በመሆን ሉዓላዊ ከሆነው የኢትዮጵያ መንግስት ጋር እንደሚሰራ አምናለሁ” በማለት ገልጸው፤ ይህም በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ሰላም ለማስፈን እንደሚያስችል ገልጸዋል።

“ለኢትዮጵያውያን ፍላጎት መሳካት ከአሜሪካ መንግስት ጋር አብሬ ለመስራት ዝግጁ ነኝ” ብለዋል።