መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት እያደረገ ያለው ጥረት ውጤት እየተመዘገበበት ነው

136

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 04/2014(ኢዜአ) መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት እያደረገ ያለው ጥረት ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ዛሬ  በሰጡት መግለጫ በኅዳር ወር በምግብ ነክ ፍጆታዎች ላይ የነበረው የዋጋ ግሽበት መሻሻል ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በህዳር ወር የምግብ ነክ የዋጋ ግሽበት 38 ነጥብ 9 በመቶ መሆኑን ገልጸው ከጥቅምት ወር ጋር ሲነፃፀር 1 ነጥብ 7 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱንም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ወራት የዋጋ ግሽበቱ ሊቀንስ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት በመንግሥት የተለያዩ እርምጃዎች እና ማሻሻያዎች ተወስደዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ የፊሲካል እና የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማሻሻል የአገር ውስጥ ምርትን ለመጨመር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የሸቀጥ አቅርቦቱን ለማሻሻል እና የገበያ አሻጥር ችግሮችን ለመፍታትም በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት ሶስት ወራት የሸቀጦች የወጪ ንግድ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ16 በመቶ ጭማሪ ማስመዝገቡንም አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ 33 በመቶው ወደ ውጪ ከተላከ የቡና ምርት የተገኘ መሆኑን ገልጸው፤ ወደ ውጪ የተላከው የቡና ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ61 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡     

በሌላ በኩል አሸባሪው ቡድን አማራ እና አፋር ክልሎች በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ንብረት ዘርፏል፤ በርካታ የመሰረተ ልማቶችን ደግሞ አውድሟል ብለዋል።

በአሸባሪ ቡድኑ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ቢሊዮን ብሮችን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም አሸባሪው ህወሃት ያወደማቸውን መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት መላ 

ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የበኩላቸውን ትብብር እንዲያደርጉ  ጠይቀዋል።  

አሸባሪው ህወሃት በወረራ በገባባቸው የአማራና አፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች 

ማህበራዊ ተቋማትን ከመዝረፍ በተጨማሪ በርካታ ንጹሃንን በመግደል፣ ሴቶችን 

በመድፈርና የተለያዩ ንብረቶችን በመዝረፍና በማውደም ጭምር አረመኔያዊ 

ድርጊቶችን ፈጽሟል።