የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶች ለመከላከያ ሰራዊት የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶች ለመከላከያ ሰራዊት የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረጉ

ታህሳስ 4/2014 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶች ለመከላከያ ሰራዊት የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረጉ።
ድጋፉንም የመከላከያ ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ማርታ ሊዊጂ ተረክበዋል።
አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 20 ሚሊዮን ብር ፣ጅማ ዩኒቨርስቲ 35 ሚሊዮን ብር፣አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ 30 ሚሊዮን ብር፣መቱ ዩኒቨርስቲ 22 ሚሊዮን ብር፣ሀሮማያ ዩኒቨርስቲ 15 ሚሊዮን ብር፣አምቦ ዩኒቨርስቲ 26 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።
በተመሳሳይ ቢ ጂ አይ ኢትዮጵያ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን የአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ቀበሌ 18 መረዳጃ እድር 200 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል።
የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ደግሞ ለመከላከያ ሰራዊት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጀ እንግዳ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ለሰራዊቱ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ የዛሬው ድጋፍ ከሰራተኛው ደሞዝና ከዩንቨርስቲው የውስጥ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው 20 ሚሊዮን የሚያወጣ የአይነት ድጋፍ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጀማል አባፊጣ በበኩላቸው የጅማ ዩንቨርሲቲ ከዚህ ቀደም ለህልውና ዘመቻው 42 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
ዛሬ ደግሞ 35 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
ዩኒቨርሲቲው ለህልውና ዘመቻው ውጤማነት የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በተያያዘም የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ለሰራዊቱ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሄር በዚህን ወቅት የትግራይ ህዝብ በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ከፍተኛ ግፍና አፈና እየደረሰበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው ከመከላከያ ጎን በመቆም የትግራይ ህዝብ ከአሸባሪው ህወሃት አፈና ነጻ እንዲሆን እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ማርታ ሊዊጂ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን ለሰራዊቱ እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አድንቀው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኀብረተሰቡ ለሰራዊቱ ከሚያደርገው ድጋፍ ጎን ለጎን በተሰማራበት የሰራ መስክ ጠንክሮ በመሰራት ለህልውና ዘመቻው ስኬት የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡