በዞኖቹ ከ284 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የደረሰ የመኽር ሰብል ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኖቹ ከ284 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የደረሰ የመኽር ሰብል ተሰበሰበ

ፍቼ/ነቀምቴ ታህሳስ 04/2ዐ14(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች ከ284 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የደረሰ የመኽር ሰብል ተሰበሰበ።
የኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋሻው አክሊሉ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ 13 ወረዳዎች ከሚገኙ 50 ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች ለአንድ ሳምንት የተሳተፉበትን የደረሰ ሰብል ስብሰባ አጠናቀዋል ።
በወረዳዎቹ 39 ሺህ 700 ተማሪዎች በቡድን በመደራጀት በ1ዐ5 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ የደረሰ ሰብል መሰብሰባቸውን ተናግረዋል ።
ሰብላቸው ከተሰበሰበላቸው መካከል አቅመ ደካማና አካል ጉዳተኛ አርሶ አደሮች እንዲሁም የዘማች ቤተሰቦች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ።
በግራር ጃርሶ ወረዳ በሰብል ስብሰባ ከተሳተፉ መካከል የፍቼ ከተማ የአብዮት ፍሬ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አያንቱ ጋሪ ኢትዮጵያ ሳትፈልግ የገባችበት ጦርነት በድል እንዲጠናቀቅ የዘማች ቤተሰቦችን መርዳት አስፈላጊ መሆኑን ተናግራለች ።
ለተማሪዎች የቀረበን ጥሪ በመቀበል በተሳተፈችበት የሰብል ስብሰባ ደስተኛ መሆኗን ገልጻለች ።
የሀገር ህልውናና ሉአላዊነትን ለማስከበር ለሚፋለሙ ዜጎች የደረሰ ሰብል ከመሰብሰብ በተጨማሪ ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ሀገሩን እየረዳ መሆኑን የገለጸው ደግሞ በፍቼ ቁጥር አንድ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ በፍቃዱ አሰፋ ነው።
የግራር ጃርሶ ወረዳ የወርጡ ቀበሌ የሚሊሻ ቤተሰብ አቶ ፉላሳ በቀለ በማሳቸው ላይ የነበረ የደረሰ ሰብል በተማሪዎችና በመንግስት ሰራተኞች በመሰብሰቡ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከ179 ሺህ ሄክታር ከሚበልጥ ማሳ ላይ የደረሰ የመኽር ሰብል መሰብሰቡን የዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታውቋል ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሉሉ ቅጣታ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ በ2013/2014 ምርት ዘመን በመኸር እርሻ 279 ሺህ 328 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለምቷል ።
እስካሁን ባለው ሂደት ከ179 ሺህ 63 ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን ተናግረዋል ።
አርሶ አደሮች፣ ተማሪዎችና የመንግስት ሰራተኞች በደቦና በተለያዩ አደረጃጀቶች በመታገዝ በሰብል ስብሰባ እየተሳተፉ መሆናቸውን አመልክተዋል ።
በዞኑ በምርት ወቅቱ ታርሶ በተለያዩ ሰብሎች ዘር ከተሸፈነው አጠቃላይ መሬት 9 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ኃላፊው አስታውቀዋል።