የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በመደገፍና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን የበኩላችንን እንወጣለን

85

ታህሳስ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በመደገፍና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ በጣሊያንና ግሪክ እንዲሁም በሮም የተመ.ድ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገለጹ።

በጣልያን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት ጣሊያንና ግሪክ ከሚገኙ እንዲሁም በሮም የተመድ ተቋማት ውስጥ ከሚሰሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ተካሂዷል።

በበይነ መረብ በተካሄደው ምክክር በየአካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረገውን ድጋፍ አስተባብሮ በሚላክበት ሁኔታ ላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የቻፓ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ሃላፊዎች ተወያይተዋል።

በሮም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሐምቢሳ ሽብርተኛው ህወሃት በሀገር አንድነት ላይ የደቀነውን ሀገርን የማፍረስ እኩይ ተግባር እና እየደረሰ ያለውን ያልተገባ የውጭ ጫና ለመመከት የዳያስፖራ ኮሚኒቲው እያደረገው ያለውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አድንቀው በአሸባሪው ህወሃት ላይ በጥምር ጦሩ እየተገኘ ያለውን ድልም ለተሳታፊዎቹ አብራርተዋል።

አምባሳደሯ በሮም፣ በግሪክ፣ በፓርማ፣ በቶሪኖ፣ በባሪ፣ ወዘተ እየተካሄደ ያለው የገቢ ማሰባሰብ በሌሎች አካባቢዎች እና ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

የገንዘብ አላላኩን በተመለከተ የአይዞን መተግበሪያን በመጠቀም በቀጥታ ድጋፉን ማዋጣት እንደሚቻል፣ በየ አካባቢው የተሰባሰቡ የድጋፍ ገንዘቦችን ወደ ኤምባሲው በመላክ በኤምባሲው በኩል ለሚመለከተው ማድረስ እንደሚቻል እና እንደ ትምህርት ቤት፣ ቤትና የጤና ተቋማትን አዋጥተን እንገነባለን ለሚሉ ደግሞ ፕሮጀክቱን በጋራ መምረጥ እና ማስረከብ እንደሚቻል አስረድተው በአፈፃፀሙም ላይ ክትትል እንደሚደረግ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተው ስለ ገንዘብ አሰባሰብ እና መላኪያ መንገዶች ገለፃ ያደረጉ ሲሆን የቻፓ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ ሃላፊዎችም ስለ አይዞን ኢትዮጵያ አጠቃቀም ገለፃ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በበኩላቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችን በመደገፍና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን የበኩላቸውን በመወጣት ሀገራችው እና ወገናቸውን ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን እንዳስታወቁ በሮም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢዜአ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም