አሸባሪው ህወሃት በ238 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ላይ ዘረፋና ውድመት ፈጽሟል

100

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 04/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በ238 የባንኩ ቅርንጫፎች ላይ ዘረፋና ውድመት መፈፀሙን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ለኢዜአ እንደገለጹት የሽብር ቡድኑ በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች በባንኩ ሰራተኛች ላይ ግድያ እንዲሁም በተቋሙ ላይ ዘረፋና ውድመት ፈፅሟል።

አሸባሪው ሃይል በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙ ስድስት ዲስትሪክት ስር ባሉ 238 የባንኩ ቅርንጫፎች ላይ ዘረፋና ውድመት አድርሷል ነው ያሉት።

ከአሸባሪው ወረራ ነጻ በወጡ አካባቢዎች የባንኩ ቅርንጫፎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው አረጋግጠናል ያሉት የባንኩ ፕሬዝዳንት በመቀሌ የሚገኙት 61 እና በሽሬ 59 የባንኩ ቅርንጫፎች ያሉበት ሁኔታ እስካሁን አይታወቅም ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ገንዘብ፣ ኮምፒተር፣ ጀነሬተሮችና ሌሎች ንብረቶችን በመዝረፍ የኤቲኤም ማሽኖችን በመስበርና በማውደም ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አብራርተዋል።

ከወራሪው ነፃ የወጡ አካባቢዎች በባንኩ ቅርንጫፎች ላይ የደረሰውን ጉዳት በዝርዝር ለማወቅና ዳግም ስራ ለማስጀመር የጥናት ቡድን ወደ ስፍራው መሰማራቱን ገልጸዋል።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ በባንኩ ቅርንጫፎች ላይ የሰነድና የንብረት ውድመት ቢደርስም የደንበኞች መረጃ ግን ሙሉ በሙሉ ማዕከል ላይ ስለሚገኝ ደንበኞች “መረጃዬ ይጠፋል” የሚል ምንም አይነት ስጋት ሊኖራቸው አይገባም።

ከአሸባሪው ህወሃት ነፃ በወጡ አካባቢዎች እስካሁን 12 የባንኩ ቅርንጫፎች ዳግም ስራ መጀመራቸውን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ ደግሞ 30 የሚሆኑትን ስራ ለማስጀመር ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም