አሲዳማ መሬታችን በመታከሙ የተሻለ ምርት እንጠብቃለን

162

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 03/2014 (ኢዜአ)፡ በአሲዳማነቱ ምርት አልባ የነበረው መሬታቸው በኖራ በመታከሙ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ በሲዳማ ክልል አርቤጎና ወረዳ በኩታ ገጠም የቢራ ገብስ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል በአርቤጎና ወረዳ አሲዳማ መሬትን በኖራ በማከምና በምርምር የተደገፉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ያመረቱትን ሰብል  አስጎብኝቷል፡፡

አሲዳማ መሬታቸው ታክሞ በ46 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም የቢራ ገብስ እያመረቱ ከሚገኙ አርሶ አደሮች መካከል ጥላሁን ሀሮ አንዱ ናቸው ፡፡

መሬታቸው በመጎዳቱ የተነሳ ከአንድ ሄክታር መሬት ከስምንት ኩንታል ያልበለጠ ገብስ ያመርቱ እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደሩ፤ አልፎ አልፎም ከዘሩት ሰብል ምርት እንዳማያገኙ ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ተስፋ በማድረግ ወደ አምራችነት መሸጋገራቸውን ጠቁመው፤  የቴክኖሎጂ ድጋፎችን ካገኙ በበጋ መስኖ ሌሎች ምርቶችን ለማምረት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ዘንድሮው ካመረቱት የቢራ ገብስ በሄክታር ከ35 ኩንታል በላይ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

አርሶ አደር ሌንጮ ዱጌ በበኩላቸው መሬታቸው በኖራ በመታከሙ የተሻለ ምርጥ እንደሚጠብቁ  ገልጸው፤42 አባወራዎችና እማወራዎች በኩታ ገጠም ተቀናጅተው መስራታቸው የባለሙያ ድጋፍና የግብርና ግብዓት በጋራ እንዲጠቀሙ እና እንዲደጋገፉ ማስቻሉን ተናግረዋል ፡፡

የምርምር ማዕከሉ ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል እንዳልተለያቸው ጠቁመው የሚደረግላቸው ድጋፍና ክትትል  ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በወረዳው ካለው የመሬት ሽፋን 68 በመቶው አሲዳማ መሆኑን የገለጹት የአርቤጎና ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በቀለ ዲካሌ ናቸው።

ችግሩ ሳይፈታ በመቆየቱ ምክንያት  አርሶ አደሮች ከሰብል ምርት ይልቅ መሬታቸውን ለከብቶች ግጦሽና መኖ ለመጠቀም መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል ችግሩን ለመፍታት ያከናወነው ተግባር ትልቅ እገዛ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ በቀለ፤ በወረዳ ደረጃም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና ተፈጥሯዊ የሥነ ምህዳር ሥራዎችን በማከናወን አሲዳማነትን ለመቀነስ  እየተሰራ  መሆኑ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስትቲዩት የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን ፊሊጶስ፤  ማዕከሉ በአርቤጎና ወረዳ በ46 ሄክታር መሬት ላይ አሲዳማ አፈርን አክሞ አርሶ አደሮችን ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር  እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሲዳማ፣ ደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በሰብል፣ በቡናና በአትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነትን የማሳደግ፣ የዝርያ ማሻሻልና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ምርምሮችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ  ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነው መሬት በአሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን አመልክተዋል።

በመስክ ጉብኝቱ ላይ የማዕከሉ ተመራማሪዎች፣  የአርቤጎና ወረዳ አመራሮችና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም