በአሸባሪው ሕወሃት የፈረሱ መሠረተ ልማቶችንና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ተዘጋጅተናል

99

ታህሳስ 3/2014/ኢዜአ/ በአሸባሪው ሕወሃት ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች የፈረሱ መሠረተ ልማቶችንና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ ማኅበር ገለፀ።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ ማኅበር "ሕይወቱን ለሰጠኝ ደሜን እሰጣለሁ" በሚል 30ኛ ዓመት የምሥረታ በአሉን ለሃገር መከላከያ ሰራዊት ደም በመስጠት አክብሯል።

የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር የሱፍ መሐመድ፤ አሸባሪው ህውሓት በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች በህዝብና መንግስት ንብረት ላይ ውድመት ማድረሱን ተናግረዋል።

በመሆኑም ያወደማቸውን የመሰረተ ልማት ተቋማት መልሶ ለመገንባት የጉዳቱን መጠን የሚያጠና ኮሚቴ ማቋቋሙን ገልጸዋል።

ከጥናቱ በኋላ በመልሶ ግንባታ ሂደት ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ አገራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ተዘጋጅቷል ብለዋል።

የማሕበሩ የሕግ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ኢንጂነር የኋላው ሲሳይ፤ አሸባሪው ህወሃት በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም ማሕበሩ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ተዘጋጅቷል ብለዋል።

ለዚሕም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽንና ዲዛይን ቢሮ ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የማሕበሩ ሰራተኞች ከገንዘብና ከቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ በዛሬው እለት ለአገር መከላከያ ሰራዊት ደማቸውን ለግሰዋል።

ደማችንን ለሰራዊታችን እየለገስን የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ተዘጋጅተናል ሲሉም የማህበሩ ሰራተኞች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም