በክልሉ በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ30 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬትን በተፋሰስ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ ነው

452

ጋምቤላ፤ ታኅሣሥ 3/ 2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ30 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ባለፈው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተተከሉት ሰባት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ችግኞች 87 ነጥብ 5 ከመቶ መጽደቃቸውም ተመልክቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ዙሪያ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ በአሸባሪው ህወሓት የተደቀነውን አደጋ ለመመከት ክልሉ ድጋፉን ከማስቀጠሉ  በተጓዳኝ የግብርና ልማት ሥራዎችን ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ ነው።

በተለይም በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ30 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ በ64 ተፋሰሶች የአፈርና ውሃ እቀባ ልማት ሥራዎች ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ባለፈው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሐ ግብር ከተተከሉት ሰባት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ችግኞች መካከል 87 ነጥብ 5 ከመቶው መጽደቃቸውን ኃላፊው አመልክተዋል።

ዘንድሮ ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሐ ግብር ከዘጠኝ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለማፍላት ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

በክልሉ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ የተጀመሩት የመሬት አስተዳደርና አየር ንብረት ፕሮጀክት አፈጻጸሞች ውስንነቶችን በማረም በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ጊዜ አፈጻጸሙን ለማሻሻል በትጋት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ኡቦንግ ኡጁሉ በሰጡት አስተያየት፤ በክልሉ እርሻና ተፈጥሮ  ሃብት ቢሮና በአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ መካከል ባለው የቅንጅታዊ አሰራር ክፍተት በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የሚታዩ ችግሮችን እንዲያርሙ ጠይቀዋል።

ሁለቱ ቢሮዎች በዓዋጅ በተሰጣቸው ሥልጣንና ተግባር መሠረት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስተያየት ሰጥተዋል።

በክልሉ ሰፊ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ የደን ሀብት ቢኖርም በህገ ወጦች ጉዳት እየደረሰ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ቲቶ ሐዋሪያት ናቸው።

ክልሉ ከደን ልማት ባሻገር ለጥበቃው ትኩረት እንዲሰጥም ጠቁመዋል።