ማዕከሉ የእንሰት መፋቂያ፣ መፍጫና መጭመቂያ ማሽን ለአርሶ አደሮች አስተዋወቀ

198

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 3/2014 (ኢዜአ) የባኮ ግብርና ምህንድስና ምርምር ማዕከል በምርምር ያገኘውን የእንሰት መፋቂያ፣ መፍጫና መጭመቂያ ማሽን ለአርሶ አደሮች አስተዋወቀ

ማዕከሉ  ማሽኑን ያስተዋወቀው በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ምክር ቤት ሴክሬታሪያት አምስተኛ ሀገራዊ የእንሰት ምርምር አውደ ጥናት ላይ ነው።

በዚህ ወቅት የማዕከሉ ዳይሬክተርና የእርሻ መሣሪያዎች ተመራማሪ አቶ ገልገሎ ኪቢ  ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የማዕከሉ  ተመራማሪዎች  እንሰት የሚቀነባበርበት ሁኔታ እና የማጓጓዣ መንገዶቹ ለምርት ብክነት፣ለድካምና ለጉዳት የሚዳርጉ መሆናቸውን በጥናታቸው አረጋግጠዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ምርምር በማዕከሉ ሜካኒካል ወርክሾፕ  ችግሩን መፍታት የሚያስችል  የእንሰት  መፋቂያ፣ መፍጫና መጭመቂያ ማሽን ማፍለቅ መቻሉን አስታውቀዋል።

ይህ የፈጠራ ስራ  ከመውጣቱ በፊት የእንሰት ስር-ሀሚቾን የሚከሰክስና የእንሰት ግንድን ለቃጫ ግብዓትነት የሚፍቅ ማሽኖች ተሰርተው  እንደነበር አስታውሰዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ማሽኖች ሲተዋወቁ  አርሶ አደሮች ጊዜያቸውንና ልፋታቸውን  እንደሚቀንስላቸው በመረዳት  መቀበላቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮች  ሁለቱንም አገልግሎት በአንድ ላይ የሚሰጥ ማሽን እንዲቀርብላቸው በጠየቁት መሰረት አዲሱ የእንሰት ማቀነባበሪያ  ማሽን ተሻሽሎ መውጣቱን  አስረድተዋል።

በማዕከሉ በምርምር ያወጣውን ማሽን ለሀዋሳ ዙሪያ እንሰት አምራች ሴቶች አስተዋውቋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ምክር ቤት ሴክሬታሪያት  የሰብል ምርምር አስተባባሪ ዶክተር ጌትነት አለማው በበኩላቸው፤ የእንስት ተክል  ከ 20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ  ዜጎች መሠረታዊ ምግብ መሆኑን ገልጸዋል።

አዲሱ ማሽን  የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም ትልቅ አቅም ያለውን የእንሰት ምርት በስፋትና በዘመናዊ መንገድ ለማልማት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ተባዝቶም  ለተጠቃሚ አርሶ አደሮች ተደራሽ እንዲሆን  ሴክሬታሪያቱ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

 የእንሰት ተክል በቴክኖሎጅ ከተደገፈ በአፍሪካ የንግድ ቀጣናዎችም ይሁን በአለም ገበያ እጀግ ተወዳዳሪ የመሆን አቅም እንዳለው የገለጹት ደግሞ የደቡብ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ለታ ጋሩማ ናቸው።

እንሰትን ለምግብነት ለማዋል የሚደረገው ጥረት በቴክኖሎጅ የታገዘ ባለመሆኑ ከ24 እስከ 25 በመቶው የእንሰት ምርት ለብክነት እንደሚዳረግ ጠቁመዋል።

 ኢንስቲትዩቱ  በምርምር በመደገፍ ዘርፉን ይበልጥ ለማበረታታትና  ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

 ከ100 በላይ የእንሰት ዝርያዎች ተሰብስበው በሽታን የመቋቋም አቅማቸው፣ ምርታማነታቸው፣በቆጮና ቡላ ጥራት ዙሪያ ምርምር እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ከምርምሩ በተጓዳኝ በምርምር ማዕከላትና በአርሶ አደሩ ተሳትፎ የእንሰት ችግኝን በስፋት የማባዛትና የማስራጨት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሀዋሳ ዙሪያ እንሰት አምራች ሴቶች ማሽኑ ስራቸውን እንደሚያቀላጥፍ በተግባር መመዕልከታቸውን ገልጸው ተባዝቶ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም