ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ክብርና ሉአላዊነት ያሳዩትን ቁርጠኝነት በልማቱም ውጤት በማስመዝገብ ሊደግሙት ይገባል

ታህሳስ 3/2014/ኢዜአ/ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ክብርና ሉአላዊነት ያሳዩትን ቁርጠኝነት በልማቱም ውጤት በማስመዝገብ ሊደግሙት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ቴክኒክ ሙያ ስልጠና እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ለአገር መከላከያ ሠራዊት እና ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ያሰባሰበውን ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለአስተዳደሩ አስረክቧል።

በርክክብ ስነ ስርአቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ከንቲባዋ፤ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ክብርና ሉአላዊነት ያሳዩትን ቁርጠኝነት በልማቱም ውጤት በማስመዝገብ ሊደግሙት ይገባል ብለዋል።

የአሸባሪውን ህውሓት አገር የማፍረስ እኩይ ዓላማ በማክሸፍ ሂደት የህዝቡ ድጋፍ፣ ትብብርና ተሳትፎ የላቀ መሆኑን አንስተዋል።

''ኢትዮጵያዊያን ለአንድ አላማ ተስማምተን ከሰራን እንዲሁም ያለንን እምቅ ሃይል እና ችሎታ ከተጠቀምን ከጉዟችን ሊገታን የሚችል ሃይል የለም" ብለዋል።

በዲፕሎማሲው፣ በኢኮኖሚና ፖለቲካው መስክ በኢትዮጵያ ላይ እየደረሱ ያሉ ተፅእኖዎችን በመቋቋምና በመመከት ያሳዩት ትብብር ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን ሃብቱ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም አገር ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ እየመከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በመዝመት፣ በመመከትና በማገዝ እንዲሁም በችግር ላይ ለሚገኙ ወገኖች በመድረስ እያሳዩት ያለው ትብብር የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ቢሮው በስሩ የሚገኙትን በማስተባበር ከ23 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት በገንዘብና በአይነት በማሰባሰብ ለዚሁ ተግባር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና የአሌክሳንድሪያ ሆቴል ባለቤት አቶ ዩሃንስ ደርሶ 5 ሚሊዮን ብር፣ በውጭ አገር የሚኖሩት አቶ በቀለ ኢረና የ100 ሺህ ዶላር እንዲሁም አርቲስት ሀመልማል አባተ የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በ3 ዙር ለመከላከያ ሰራዊቱና ለተፈናቃዮች ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚደርስ የሃብት ማሰባሰብ መቻሉ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም