ከሸዋ ሮቢት ከተማ የተዘረፈ የሕዝብና የመንግሥት ንብረት እያስመለስኩ ነው-እዙ

95

ደብረ ብርሃን ታህሳስ 03/2014(ኢዜአ) በአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ ቡድኖች ከሸዋ ሮቢት ከተማ የተዘረፈ የሕዝብና የመንግሥት ንብረት ማስመለስ መጀመሩን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ እዝ አስታወቀ።

የእዙ አባል የሆነው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ የሸዋ ሮቢት ኮማንድ ፖስት አዛዥ ኢንስፔክተር እንዳልካቸው አስገልጠው ለኢዜአ እንደገለጹት ኮማንድ ፖስቱ በአሸባሪዎቹ የተዘረፈውን ንብረት ከሸዋ ሮቢትና ከኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ህብረተሰብ ጋር በመቀናጀት እያስመለሰ ነው።

ከተመለሰው ንብረት ውስጥ 20 ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ ባጃጆች፣ 14 ሞተር ሳይክሎች፣ ከ60 በላይ ቢስክሌቶችና  ቴሌቪዥኖች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

እንዲሁም 95 የቀንድ ከብቶች፣ 110 በግና ፍየሎችና ፈረሶች መመለሳቸውን ተናግረዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ የተዘረፉት ንብረቶቹ ያሉበትን ቦታ በማመላከት ትብብር እያደረገ መሆኑንም ኢንስፔክተር እንዳልካቸው ተናግረዋል።

ቀሪ የሕዝብና የመንግሥት ንብረት ለማስመለስ ጥረቱ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የሸዋ ሮቢት ከተማ የአገር ሽማግሌ አቶ ኢሳይያስ ተሰማ በበኩላቸው የሃብት ማስመለስ ሥራ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እንደሚያስችል ገልጸዋል።

አሸባሪዎቹ ቡድኖች በአጎራባች ሕዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም፤በሕዝቦቹ መካከል  ለዘመናት በዘለቀው የአብሮነት ባህል እንዳይሳካላቸው ማድረጉን አስታውቀዋል።

''በቀጣይም የተበተኑ የቡድኖቹ አባላትን ለመንግሥት በማስረከብ ሰላማችን ማረጋገጥ ይኖርብናል'' ብለዋል።

በአሸባሪው ህወሃት ተይዞ የቆየው ሸዋ ሮቢትና አካባቢው በአገር መከላከያ ሠራዊትና በፀጥታ ሃይሎች ነፃ መውጣቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም