“ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል እወርዳለሁ” ያለው አሸባሪውን ህወሃት በጋራ መክተን ወደተመኘው ሲኦል ለመሸኘት እንሰራለን

258

ታህሳስ 3/2014/ኢዜአ/”ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል እወርዳለሁ” ያለውን የህወሃት አሸባሪ ቡድን በጋራ መክተን ወደተመኘው ሲኦል ለመሸኘት እንሰራለን ሲል የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ እስትንፋስ የሆነውን የአገር መከላከያ ሰራዊት መደገፍ የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብሏል።


የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በግንባር በመገኘት ለመከላከያ ሰራዊት ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የዓይነት ድጋፍ አስረክቧል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ አበበ፤ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል እወርዳለሁ” ያለውን የህወሃት አሸባሪ ሃይል በጋራ መክተን “እራሱን ወደ ሲኦል ለመሸኘት” እንሰራለን ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ እኩይ ዓላማ እየከሸፈ በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በመደምሰስ ላይ መሆኑን እየተመለከትን ነው ብለዋል።

በመሆኑም ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት ለቆመው የአገር መከላከያ ሰራዊትን መደገፍ የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ፤ “ኢትዮጵያ በመንደር ሽፍታና አሸባሪ ሃይል ፈፅሞ አትፈርስም፤ ክብሯና ሉአላዊነቷ ተጠብቆ ይቀጥላል” ብለዋል።

“ኢትዮጵያውያን ለነፃነታቸውና ለክብራቸው ወደ ኋላ የማይሉ አናብስቶች በመሆናቸው” አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ተደምስሶ አገር የማፍረስ ህልሙ ቅዥት ሆኖ ይቀራልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያን በተለያዩ አጋጣሚዎች ለመውረር የሞከሩ የውጭ ሃይሎች ሁሉ ተሸንፈው መመለሳቸውን ያስታወሱት ዶክተር አረጋዊ የውስጥ ባንዳ ሆኖ የተነሳው አሸባሪው ህወሃትም አከርካሪው ተመቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ /ኢሶዴፓ/ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው አሜሪካና አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት አሸባሪውን ህወሃት በመደገፍ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ላይ ያልተገባ ጫና ማሳረፋቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም የሽብር ቡድኑን ለመደገፍ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ እውነትን የያዙ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አሸናፊነት አውን እየሆነ መጥቷል ብለዋል።

የፓርቲዎቹ የጋራ ምክር ቤት በግንባር በመገኘት ለመከላከያ ሰራዊት ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የዓይነት ድጋፍ አድርጓል።

በተያያዘ ዜና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በግንባር በመገኘት ለሰራዊቱ የ10 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የዓይነት ድጋፍ አድርጓል።

የኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ፤ አሸባሪው ህወሃት ተቋማትን በማውደም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያደረገውን ሙከራ በማክሸፍና ቡድኑን በመደምሰስ የመልሶ ግንባታውን እውን እናደርጋለን ብለዋል።