ሚኒስቴሩ ለተፈናቃዮች 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ

169

ደብረ ታቦር ታህሳስ 3/2014(ኢዜአ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ተፈናቅለው በባህርዳር ለተጠለሉ ተፈናቃዮች 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ ዛሬ አደረገ።

ከድጋፉ ብትን ጨርቅ፣ ጫማዎች፣ ምግብና የልብስ ማጠቢያዎች ይገኙበታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፤ ተፈናቃይ ወገኖችና የጸጥታ ኃይሎችን በራስ አቅም መደገፍ ይገባል ብለዋል።

የውጭ ጣልቃ ገብነትና ጫናውን በመቋቋም የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስቀጠል ዲያስፖራውን ጨምሮ ተጠሪ ተቋማት የሚያደርጉት ያልተቋረጠ ተሳትፎ ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የህዝብ  ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢያሱ መስፍን በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

መንግሥት የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ለተፈናቃዮች የዕለት ደራሽ ምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ቢሞክርም፤ ከተፈናቃዮች ቁጥር አንጻር ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት በርካታ አካባቢዎች  ነጻ እየወጡ በመሆናቸው ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋም ቀጣዩ የቤት ሥራ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በክልሉ በአሽባሪው ህወሃት ወረራ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መፈናቀሉን  ኃላፊው አመልክተዋል።