ወጣቱ የአገር መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል የሃገር ሉአላዊነትን ሊያስጠብቅ ይገባል

73

ታህሳስ 3/2014 (ኢዜአ )ወጣቱ የአገር መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል የሃገር ሉአላዊነትን ሊያስጠብቅ ይገባል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስገነዘቡ።

ከክልሉ ከተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ ወጣቶች በሃገራዊና ክልላዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በባህር ዳር ከተማ እየመከሩ ነው ።

በምክክር መድረኩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ሌተናል ጀነራል ሃሰን ኢብራሂም፣የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በመድረኩ ላይ እንዳሉት አሸባሪው ህወሃት ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ንፁሃን ዜጎችን በግፍ ገድሏል፤የህዝብ ሃብትና ንብረትም አውድሟል።

አሸባሪው ቡድን ሃገርን ለማፍረስ አላማ አድርጎ የተነሳ መሆኑንም ጠቁመዋል ።

አሸባሪው ህወሀት የያዘው ሀገር የማፍረስ ሴራም በኢትዮጵያ ህዝቦች የተባበረ ክንድ እየከሸፈ መሆኑን አመልክተዋል።

"ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከቆሙ የሚያሸንፋቸው እንደሌለም በአጭር ጊዜያት በህወሃት ላይ የደረሱት ሽንፈቶች አመላካች ናቸው" ሲሉም ተናግረዋል።

"አሁን ላይ የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ የተነሱበት ወቅት ነው"ያሉት አቶ ገዱ በተለይም ወጣቱ የሃገር መከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል የሃገርን ሉአላዊነት በማስጠበቅ እንደ አባቶቹ ታሪክ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሌተናል ጀነራል ሃሰን ኢብራሂም በበኩላቸው "ሃገር አፍራሹን ጠላት በዘላቂነት ለማምከን ወጣቱ የሃገር መከላከያ ሰራዊቱን ሊቀላቀል ይገባል" ብለዋል።

"ሃገሪቱ ላይ የተጋረጠውን ስጋት ለመቅረፍ የወጣቱ የሃገር መከላከያ ሰራዊትን መቀላቀል አይነተኛ አማራጭ ነው " ሲሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም