የአፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና መኖር የህልውና ጥያቄ ነው

62

ሚዛን አማን፤ ታህሳስ 3/2014 (ኢዜአ)፡ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና እንዲኖራት የተነሳው ጥያቄ የአፍሪካ ህልውና ጥያቄ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ።

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የፓለቲካል ሳይንስና የታሪክ ምሁሩ ዶክተር ንጉስ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዳይኖራት መደረጉ የዳር ተመልካችነትን ፈጥሮ ቆይቷል።

በአፍሪካ ጉዳይ ላይ የሚወስኑት ኃያላን ሀገራት እንጂ አፍሪካዊያን ስለራሳቸው ጉዳይ መወሰን እንዳይችሉ መደረጋቸው  ቅራኔን ሲፈጥር የቆየ መሆኑን ተናግረዋል።

ሮበርት ሙጋቤ ''በራሳችን ጉዳይ እኛ መወሰን አለብን'' ብለው ጥያቄ ሲያነሱ ከነበሩት የቀድሞ የአፍሪካ መሪዎች መካከል እንደነበሩ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት የአፍሪካ ሀገራት ጥያቄውን ማንሳታቸው ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው "ጥያቄው አወንታዊ ምላሽ እንዲያገኝ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ጥንካሬ ወሳኝ ነው" ብለዋል።

በመሆኑም የአፍሪካ ሀገራት በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ አጀንዳውን በማንጸባረቅ ትግል ማድረግ እንደሚገባ  ጠቁመዋል።

"ምላሹ በአፍሪካ መሪዎች እጅ ነው" ያሉት ዶክተር ንጉስ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ጥያቄውን ማቀጣጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት አዳነ ኮርቦ በበኩላቸው ከኤዥያ ቀጥሎ ትልቋ አህጉር አፍሪካ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ህዝብ ይዛ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ ሳታገኝ መቆየቷ በርካታ ተፅዕኖዎችን እንዳስከተለባት አስታውሰዋል።

ቋሚ የጸጥታው ምክር ቤት አባላት የአፍሪካን ነባራዊ ሁኔታና እውነታ ከማገናዘብ ይልቅ ለራሳቸው በሚጠቅም መልኩ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ሲሰጡ እንደቆዩ አስረድተዋል።

"አፍሪካ ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን ያለውን ወንበር እስካላገኘች ድረስ ጥቅሟ ሊከበር አይችልም" ያሉት ምሁሩ፤ አፍሪካውያን አሁን የተነሳውን ጥያቄ አጀንዳቸው አድርገው የሚገፉ ከሆነ ውጤት ሊያስገኝ የሚችል ተገቢ ጥያቄ መሆኑን አመልክተዋል።

"አፍሪካ እንደ ትልቅ አህጉር በምክር ቤቱ ቋሚ ውክልና ያለማግኘቷ ኢ-ፍትሃዊነትን የሚያንጸባርቅ ነው "ያሉት ምሁሩ፤ በዲሞክራሲ ሥርዓት ተወካይ ማስቀመጥ ግዴታ መሆኑን ጠቁመዋል።

"እኛ አፍሪካውያን በፓን አፍሪካኒዝም ተቃኝተን በአንድነት ቆመን ከታገልንና ከበረታን ተደማጭነትን እናገኛለን" ብለዋል።

ምሁራኑ ጥያቄው እልባት ሲያገኝ በራስ ጉዳይ የሌላን ውሳኔ የመጠበቅ ተጽዕኖን የሚሽር መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም