ኢትዮጵያ አፍሪካውያንን ለነጻነት የማንቃት ታሪካዊ ልምድ አላት-የኢትዮ-ነብዩ መስፍን የኢትዮ-አሜሪካውያን ካውንስል ተባባሪ መስራች

232

ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ አፍሪካውያንን ለነጻነት የማንቃት ታሪካዊ ልምድ ያላት ሀገር ናት ሲሉ የኢትዮ-አሜሪካውያን ካውንስል ተባባሪ መስራች አቶ ነብዩ መስፍን ተናገሩ፡፡

ከስፑትኒክ ዓለም አቀፍ ራዲዮ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ነብዩ መስፍን ኢትዮጵያ በአፍሪካውያንም ዘንድ ትልቅ ቦታ እንዳላት ገልጸዋል።

በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ነጻነታቸውን ያገኙት ኢትዮጵያ ነጻ ሆና በመቆሟ ብቻ ሳይሆን ሀገራቱ ለነጻነታቸው በሚያደርጉት ትግል ወቅት ተገቢውን ድጋፍ ከኢትዮጵያ በማግኘታቸውም ጭምር ነው ብለዋል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ ላይ አዲስ የቅኝ ግዛት አጀንዳ ለማራመድና ጣልቃ በመግባት ለማፍረስ የሚሞክሩ አካላት ይህንን ታሪክ ካለመረዳታቸው የተነሳ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ነብዩ አክለውም አሁን እየታየ ያለው የ’በቃ’ ‘#NoMore’ ዘመቻ ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲይዝ የተደረገው በኢትዮጵያ ጠንሳሽነት መሆኑን በማሳያት አቅርበዋል፡፡

በዘመቻው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በጋራ መቆማቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ህዝባዊ ቅንጅቱ የተፈጠረው አሜሪካም ሆነች ሌሎቹ ሀገራት የኢትዮጵያን እውነት አልሰማ በማለታቸው እንደሆነ የገለጹት አቶ ነብዩ፤ ዘመቻው አሁን መልካም ውጤት እየተገኘበት መጥቷልም ብለዋል፡፡

የአሜሪካም ሆነ የአንዳንድ ምዕራባውያን ጣልቃ የመግባት ፍላጎት ዋና ምክንያት ዕምቅ ማዕድናትን ለመቀራመት ፍላጎት የሚመነጭ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

ይህን ድብቅ ፍላጎት በሚገባ የተረዳው በውጭ የሚገኘው የኢትዮ-አሜሪካ እና ኤርትራ አሜሪካውያን ዜጎች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ተደራጅተው በመንቀሳቀሳቸው ውጤት እያመጡበት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ሀገራት ልክ ሌሎች ሀገራትን ለማፍረስ የተጠቀሙበትን የተሳሳተ መረጃ የማሰራጨት ስልት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባትና ለማፍረስ መጠቀማቸውን አስታውሰዋል፡፡

አቶ ነብዩ ቲውተርን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የ’በቃ’ ዘመቻን በማፈን ለአሜሪካም ሆነ ለሌሎቹ መሪዎቻቸው ያላቸውን ፖለቲካዊ ታማኝነት አሳይተዋል ብለዋል፡፡

አንዳንዶቹ ስለኢትዮጵያ የተሳሳተ ግንዛቤ በማሰራጨት ዜጎቻቸውንና ሌሎች አፍሪካውያንን ለመዋሸት ቢሞክሩም እውነታውን እየተረዱ በመምጣታቸው ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም እንቅስቃሴውን መቀላቀላቸውን ጠቅሰዋል፡፡  

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ግንባር መዝመት በአሜሪካ፣ በምዕራባውያንና በሌሎችም አካላት የነበረውን ኢትዮጵያን የማፍረስ ዕቅድና ፍላጎት መና ማስቀረቱን ድሎቹን ዋቢ በማድረግ ጠቅሰዋል፡፡

አሸባሪው ህወሃት በከባድ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ በመዘፈቁ ከአሜሪካ በሚስጥር ሲደረግለት የነበረውን ድጋፍ እና አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላት ትክክለኛ ፍላጎት ምን እንደሆነ በይፋ እንዲናዘዝ አስገድዶታል ብለዋል፡፡

አቶ ነብዩ በመጨረሻም የሽብር ቡድኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚመሩት ጥምር ጦር የሚሰነዘርበትን ከባድ ምት መቋቋም ሲያቅተው ሆን ብሎ የህዝብ መገልገያ መሰረተ-ልማቶችን በተለይ ሆስፒታሎችን እያወደመ፣ ከባድ ኢ-ሰብዓዊ ጥቃቶችንና ወንጀሎችን እየፈጸመ ለመሸሽ መገደዱን አንስተዋል፡፡

ለዚህም አምንስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትስ ዎች የመሳሰሉ ድርጅቶች በሽብር ቡድኑ የተፈጸሙ ኢ-ሰብዓዊ ወንጀሎችን በሪፖርታቸው እያወጡ መሆኑን ለአብነት አቅርበዋል፡፡   

በቆይታቸውም ኢትዮጵያ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ነጻ መውጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገች ሀገር መሆኗን አስታውሰዋል፡፡ 

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።