የልማት ተቋማት የህዝቡን ኑሮ ለመለወጥ ሰፊ ስራ ይጠብቃቸዋል

198

ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የልማት ተቋማት ያለውን ሀብት፣ እውቀትና ጉልበት በመጠቀም የህዝቡን ኑሮ ለመለወጥ ሰፊ ስራ እንደሚጠብቃቸው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

“ተወዳዳሪና ውጤታማ የሆኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ለብልፅግናችን” በሚል መሪ ሐሳብ የኦሮሚያ ክልል የመንግስት የልማት ድርጅቶች የንቅናቄ መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ባደረጉት ንግግር፤  የልማት ተቋማት መቋቋም ዋነኛው ዓላማ የገበያ እጥረትን መፍታት፣ ተወዳዳሪነትን  መፍጠር፣ ገቢን ማሳደግና የህዝብና የመንግስትን አቅም ማሳደግ ነው ብለዋል።

“ህዝባችን በድህነት የቆየው በሳይንሱ የምናውቀውንና የምናወራውን እውቀት ወደ ተግባር መለወጥ ባለመቻላችን ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የልማት ተቋማት ያለውን ሀብት፣ እውቀትና ጉልበት በመጠቀም የህዝቡን ኑሮ ለመለወጥ ሰፊ ሰራ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ለሁለንተናዊ ልማት ህዝብን ማሳተፍ፣ የግል ሴክተር በስፋት መጠቀምና የመንግስትን አቅም በማቀናጀት ወደ ተጨባጭ ስራ መግባት ደግሞ የህዝባችንን ኑሮ ለመለወጥ በዋነኛነት ያሉን ሶስቱ አቅሞች ናቸው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

የኦሮሚያ ክልል የመንግስት የልማት ተቋማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ኮከቤ ድዳ በበኩላቸው፤  ከልማት ተቋማቶቻችን የሚጠበቀውን ውጤት ለማግኘት ተቋማቱ ከቢሮው ጋር ያላቸውን ትስስር ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።

ትስስሩን ለማጠናከር ይረዳ ዘንድም መሰል የንቅናቄ መድረክ ተዘጋጅተዋል ያሉት ሃላፊዋ፤ ተቋሙ እራሱን ችሎ በቢሮ ደረጃ ከተቋቋመ ወዲህ ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች መፍታት ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን  ገልጸዋል።

በመድረኩ የኦሮሚያ ክልል የመንግስት የልማት ድርጅቶች ያሉበትን ተጨባጭ ሁኔታ አስመልክተው ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ  የመንግስት ንብረት አስተዳደር ክላስተር ሃላፊ ዶክተር ግርማ አመንቴ የልማት ተቋማት ውጤታማ እንዲሆኑ ተልዕኳቸውን መፈጸም እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ይህ ከሆነ ግባቸውን ይመታሉ ብለዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።