ተጎጂዎችን ከመደገፍ እስከ ማቋቋም ድረስ ትብብሩ እንዲጠናከር ጥሪ ቀረበ

170

ሰመራ፣ ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ሀገርን ከጠላት ጥቃት ለመታደግ ያሳዩትን ተነሳሽነት በቀጣይም ተጎጂዎችን ከመደገፍ እስከ መልሶ ማቋቋም ድረስ እንዲያጠናክሩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ጥሪ አቀረቡ።

አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል በፈጸመው ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር እንዲሁም የጉምሩክ ኮሚሽን ዛሬ ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

በድጋፍ ርክክቡ ወቅት ዶክተር ኤርጎጌ  ሕብረታችንን ካጠናከርን አሸባሪው ህወሓትና ከጀርባው ተሰልፈው በሀገራችንና በህዝባችን ላይ ያሴሩ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን እንደምናሸንፍ በአውደ ግንባር የታዩ ውጤቶች ምስክር ናቸው ብለዋል።

አንዳንድ የምዕራባዊያን በተለያየ የኢኮኖሚያዊ አሻጥርና ጫናዎች ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ለማንበርከ እየጣሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን ከጠላት ጥቃት ለመታደግ ያሳዩትን ተነሳሽነት በቀጣይም ተጎጂዎችን ከመደገፍ እስከ መልሶ ማቋቋም ድረስ እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የህዝቡን ነባር የአብሮነትና የመረዳዳት አኩሪ ባህላዊ እሴት ዛሬም አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

በተለይም አረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን፣ ሴቶችና ህጻናትን ለመደገፍ ከመንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ባለፈ ሁሉም ህብረተሰብ የአቅሙ ማድረግ እንዳለበት አመልክተዋል።

ሚኒስቴሩ በአፋር ለተፈናቀሉ ወገኖች የ5 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እንዲሁም 31 ሚሊዮን ብር የሚገመት የተለያዩ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አድርገዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበቶ በበኩላቸው፤ኮሚሽኑ የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዳደረገ ጠቁመዋል።

በቀጣይም ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ከክልሉ መንግስት ጎን በመቆም ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ብርሃኑ አበበ በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ነው የገለጹት።

በአፋር ክልል በጦርነት የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ የሚውል የ5 ሚሊዮን ብር ማበርከታቸውንና በቀጣይም  የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

የአፋር ክልል  በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል የሃብት አሰባሳቢ አብይ ኮሜቴ ሰብሳቢ አቶ መሀመድ አህመድ፤ አሸባሪው ህወሓት በሀገር ላይ የደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ ኢትዮጵያዊያን አኩሪ ተጋድሎ እየፈጸሙ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፋር ህዝብ ሚሌን  ለመያዝ አሰፍስፎ የመጣውን ጠላት ከወገን ጦር ጋር በመሆን አንገቱን ደፍቶ እንዲመለስ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ሁሉም ክልሎችና ተቋማት ከክልሉ መንግስትና ህዝብ ጎን በመቆም ያሳዩት ወገናዊ አጋርነት በክልሉ መንግስትና ህዝብ ሁሌም እንደማይረሳ ተናግረዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።