በአሸባሪው ህወሃት የወደሙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ በማደራጀት ወደሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው

283

ደብረ ብርሃን፣ ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሃት የወደሙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ በማደራጀት ወደሥራ ለማስገባት እየተሰራ እንደሚገኝ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ።  

ከአሸባሪው ህወሃት ወረራ ነጻ የወጡ አካባቢዎች ፈጥነው ወደ መደበኛ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረው መንግስት ዓቅም በፈቀደ መጠን ተቋማት በፍጥነት ወደ አገልግሎት እንዲገቡ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋሮቢት ከተማ በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ህዝባዊ ውይይት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ቡድኑ ፀሐይ እየጠለቀችበት ነው።

ከወረራ ነፃ የሆኑ አከባቢዎች ፈጥነው ወደ መደበኛ የእለት ተለት እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸው፤ “መንግስት አቅም በፈቀደ  አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ በማደራጀት ወደሥራ የሚገቡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየሰራ ነው” ብለዋል።

በሸዋ ሮቢት ከተማ ማህበረሰቡና ነጋዴዎች የአካባቢያቸውን ሰላም ከመጠበቅ ጎን ለጎን አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በመክፈት ሥራ ሊጀምሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

አሸባሪውን ህወሓትና ተላላኪዎቹ በህዝብ ላይ ያደረሱት በደል የማይረሳ ጠባሳ መጣሉን ገልጸው፤ ቡድኑን መዳረሻ ለማሳጣት እየተደረገ ባለው ትግል ህብረተሰቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረጻደቅ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋምት ወደ ሥራ እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በህወሓት ተስፈኞች የተዘረፈውን የንፁሀን ሀብት ለማስመለስ መንግስት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ህብረተሰቡ የተደበቁ ተላላኪ ባንዳዎችን ማጋለጥ እንዳለበት አመልክተዋል።

“የሽብር ቡድኑ የፈጸመውን በደል ባንረሳውም አንድነትን በማጠናከርና ከቁዘማ በመውጣት ሥራ መጀመር አለብን” ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ምሱጦፋ ሼሁ ናቸው።

የአካባቢውን ሰላም ከመጠበቅ ጎን ለጎን በጦርነቱ የተቀዛቀዘውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እንስራለን” ሲሉም አክለዋል።

የአካባቢያቸውን ሰላም በማረጋገጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ ሁሉም በተሰማራበት ስራ መጀመር አስፈላጊ መሆኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

ለዚህም የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል። 

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።