በአደጋ ጊዜ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የጤና አገልግሎት ስርአት መገንባት ያስፈልጋል

158

ጅማ፣ ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለችግሮች የማይበገርና በአደጋ ጊዜ ለሁሉም ህብረተሰብ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የጤና አገልግሎት ስርአት መገንባት ያስፈልጋል ሲል የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ የጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ለጤና ባለሙያዎች ለድንገተኛ ክስተቶች የማይበገር የጤና አገልግሎት ስርአት ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

የጤና አገልግሎት ስርአቱ መገንባት ለሚከሰቱ የድንገተኛ ወረርሽኝ የጤና እክሎች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ እንዳሉት፤ በመደበኛው የጤና አገልግሎት ስርአቱ የድንገተኛ ጊዜ ወረርሽኝንም ሆነ ሰው ሰራሽ አደጋ ሲፈጠር ፈጣን ምላሽ ለመስጠት አዳጋች ነው።

ከአለም ጤና ድርጅትና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የጤና ባለሙያዎች ጋር ምክክር ተደርጎ በሙከራ ደረጃ የሚተገበርና ከስልጠናው በኋላ በቀጥታ የሚዘረጋ የጤና ስርአት ለመገንባት ያለመ ምክክር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

“ለትግበራው በጅማ ከተማና በአካባቢው ለሚገኙ  የጤና ተቋማት ሰልጣኞች በሚሰጡት መረጃዎች መሰረት የግብአት፣ የሰው ሃይልና የስልጠና ክፍተቶች ተሟልተው የአደጋ ጊዜ ማእከላት ይቋቋማሉ” ብለዋል።

የጤና ስርአት ግንባታ ስልጠናውን የሰጡት ዶክተር በላይ ማካንጎ በበኩላቸው የጤና አገልግሎት ስርአቱ ለሚፈጠሩ የተለያዩ የጤና እክሎች ቀድሞ በመዘጋጀት አገልግሎቱን  ለሁሉም ህብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ መሆኑን አመልክተዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈትያ አወል በበኩላቸው የጤና ባለሙያዎች በአደጋ ጊዜ ችግሮችን ተቋቁመው ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ የሚያስችላቸውን ግንዛቤ እንዲጨብጡ ለማድረግ ስልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።