የኢንስቲትዩቶቹ አመራሮችና ሰራተኞች በሱሉልታ ከተማ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ሰበሰቡ

219

ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሠራተኞች በሱሉልታ ከተማ የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ሰበሰቡ።

በተጨማሪ ተቋማቱ ለዘማች ቤተሰቦች የምግብ ነክ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

የኢትዮጰያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ ለኢትዮጵያ ክብርና ነጻነት ሲሉ ለሚዋደቁ የኢትዮጵያ ጀግኖች ደጀንነታችንና ድጋፋችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ብለዋል።

ከዚህ አኳያ የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል በመሰብሰብ ደጀንነታቸውን በተግባር ማሳየታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዘማቾችን ቤተሰብ በምንችለው ሁሉ መደገፍ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ ናቸው።

የኢንስቲትዩቱ አመራሮችና ሰራተኞች የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል ከመሰብሰብ በተጨማሪ የምግብ ነክ ቁሳቁስ ደጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ  እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የተቋማቱ ሰራተኞች በበኩላቸው ለአገር ህልውና ዘብ ለሆኑት የዘማች ቤተሰቦችን በመደገፍ አለኝታነታቸውን በተግባር እንደሚያረጋግጡ ገልጸዋል።

ዶክተር ኃይሉ ዳዲ፤ ኀብረተሰቡ ለሰራዊቱ ከሚያደርገው ደጀንነት በተጨማሪ በተለያዩ ግንባሮች ተሰልፎ ለአገሩ ህልውና ሚናውን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የዘማች ቤተሰቦች ለመደገፍና በተግበር ያላትን አጋርነት ለመግለጽ በሰብል ስብሰባ መርሃ ግብሩ መሳተፏን የተናገረችው ደግሞ ወይዘሪት ቤተልሄም ንጉሴ ናት፡፡

አቶ አብይ ግርማ በበኩላቸው፤ የዘማች ቤተሰብን ሰብል መሰብሰብ የህልውና ዘመቻው አንደኛው ግንባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሱሉልታ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አቡ ቢርኪ በበኩላቸው በከተማው የዘማቹን ቤተሰብ ለማበረታት የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ፣ ለተማሪዎች ትምህርት ቁሳቀሱስ ማሟላትና የምግብና ምግብ ነክ ድጋፎች እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በከተማዋን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ በተደራጀ መልኩ ኅብረተሰቡ አካባቢውን እየጠበቀ እንደሚገኝ ተናግረዋል።  

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።