“የበቃ” እንቅስቃሴ ተጽእኖ ፈጣሪ የአፍሪካውያን ድምጽ እየሆነ መጥቷል

246

ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) “የበቃ” ወይም ‘ #NoMore’ እንቅስቃሴ ተጽእኖ ፈጣሪ የአፍሪካውያን ድምጽ እየሆነ መምጣቱን ኢዜአ ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ የሚኖሩ ‘ራስታፋሪያኖች’ ገለጹ።

‘ራስታፋሪያኑ’ ኦርላንዶ ቶማስ “የበቃ” ወይም ‘ #NoMore’ እንቅስቃሴ እንደ ‘ብላክ ላይፍስ ማተር’ በቅርብ ዓመታት ከታዩ ዓለም አቀፍ ዘመቻዎች መካከል በዋናነት ሊጠቀስ እንደሚችል ገልጿል።

እንቅስቃሴው ኢትዮጵያን ጨምሮ በሰሜን አሜሪካ፣ አፍሪካና ሌሎች የዓለም ከተሞች መሰራጨቱን ተናግሯል።

“የበቃ” ወይም ‘ #NoMore’ እንቅስቃሴ “በአሁኑ ትውልድ በአፍሪካ ውስጥ እየተሰማ ያለ ትልቅ ድምጽና ሃይል ያለው ንቅናቄ ነው” ብሏል ኦርላንዶ። 

ራስ ሃይሌ ታይገር ስላሴ አፍሪካውያን የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የመፍታት አቅማቸውን ይበልጥ ሊያሳድጉ እንደሚገባ ገልጿል።

አፍሪካውያን ንግድን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የእርስ በርስ ግንኙነት ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግሯል።

“ኢትዮጵያ በዓለም ቅኝ ያልተገዛች አገርና የረጅም ጊዜ አኩሪ ታሪክ ያላት ናት” ስትል የገለጸችው ደግሞ ሌላኛው ራስታፋሪያን ካሮል ሮኬ ናት።

ኢትዮጵያውያን ለብዙ 100 ዓመታት ለመብቷና ለነጻነቷ የታገለች አገር እንደሆነችና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ የራሷን ጉዳዮች በራሷ የመፍታት አቅም እንዳላት በመገንዘብ ጣልቃ ገብነቱን ሊያቆም ይገባል ብላለች።

በመላው ዓለም የሚኖረው የራስተፋሪያን ማህበረሰብ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ጨምሮ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ከኢትዮጵያ ጎን መሆኑን ማሳየት እንደሚጠበቅበት ገልጻለች።

ራስታፋሪያን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የኢትዮጵያ መንግስትና ለኢትዮጵያን እድገት  አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ካሮል ሮኬ የገለጸችው።

በጃማይካ የሚኖሩ ‘ራስታፋሪያኖች’ ‘የበቃ #NoMore’ ዘመቻ ሰላማዊ ሰልፍ ትናንት ኪንግስተን በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት ያካሄዱ ሲሆን፤ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

‘ራስታፋሪያን’ በጃማይካ በ1930ዎቹ ዓ.ም የተነሳ እንቅስቃሴ፣ እምነትና የአኗርኗር ዘይቤ ነው።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።