በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመራው ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ዋናውን የወልድያ መቀሌ ጎዳና ቆርጦታል፡፡

58

ሰበር ዜና

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት፣ በአሸባሪው ወራሪ ላይ በሰነዘሩት ክንደ ብርቱ ማጥቃት፣ በምሥራቅ ግንባር ስትራቴጂያዊ የሆኑትንና ወራሪው በፍጻሜ ዋዜማ ላይ መሆኑን የሚያሳዩትን የዞብል ሠንሠለታማ ተራሮችን ጨምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የአርጆ፣ ፎኪሳ እና ቦረን ከተሞችን ተቆጣጥሯል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የጉራ ወርቄ አካባቢዎችን በመቆጣጠር የወልድያ መቀሌ ዋናውን አውራ ጎዳና በመቁረጥ ጠላት መውጫ አጥቶ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚሁ ግንባር የድሬ ሮቃና የሶዶማ ከፍተኛ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ከተሞችና ተራሮች በመቆጣጠር ጥምር ጦሩ ወደ ሐራ ከተማ እየገሠገሠ ይገኛል፡፡

በውጫሌ ግንባር ደግሞ የአምባሰል ከፍተኛ ሠንሠለታማ ተራሮችን ጨምሮ የሮቢትና የጎልቦን፣ በወረባቦ ወረዳ የሚሌ ኮትቻን፣ በሐብሩ ወረዳ የኮልቦን፣ የመርካታና የፋጂን አካባቢዎችን በመቆጣጣር ወደ መርሳ ከተማ እየገሠገሠ ነው፡፡

በእነዚህ ግንባሮች በተደረገው ኦፐሬሽን በአሸባሪው የጠላት ኃይል ላይ በተሠነዘረበት ማጥቃት ጠላት ሙት፣ ቁስለኛና ምርኮኛ ሆኗል፡፡

የወገን የመካናይዝድ ኃይልና ንሥሮቹ የአየር ኃይሉ በጥምረት ባካሄዱት ኦፐሬሽን የጠላት ኃይል ምንም ዓይነት ተሸከርካሪ እና ከባድ መሣሪያዎችን ይዞ እንዳይንቀሳቀስ ስላደረጉት፣ ጠላት በየአቅጣጫው ጥሎ ለመፈርጥጥ ተገድዷል፡፡

ለበርካታ ቀናት ያከማቻቸውን ቁስለኞችንም ጥሎ ፈርጥጧል፡፡ የዘረፈውን ንብረትም በየቦታው እያዝረከረከ እግሬ አውጪኝ በማለት ላይ ይገኛል፡፡

ጠላት ዋናው የቆቦ ወልድያ መንገድ ስለተዘጋበት በድንብርብር በጋሸና ላሊበላ በኩል ለማምለጥ ከፍተኛ ትንቅንቅ ቢያደርግም በወገን ጥምር ጦር እንደ ቅጠል ከመርገፍ አልተረፈም፡፡

በወረራ ውስጥ የቆየው ኅብረተሰብ በከፍተኛ ወኔና ጀግንነት በመነሣሣት ከወገን ጦር ጋር ተባብሮ በመሰለፍ አኩሪ ተጋድሎ ፈጽሟል፡፡

አሁንም ክንደ ብርቱውን የወገን ጥምር ጦር መቋቋም አቅቶት በየጢሻው የተበተነውን የአሸባሪውን ጀሌ፣ የየአካባቢው ሕዝብ በመማረክ፣ እምቢ ያለውንም በመደምሰስ የጀግንነት ተግባሩን እንዲፈጽም መንግሥት ጥሪ ያቀርባል፡፡

ነጻነታችንን የምናረጋግጠው በተባበረ ክንዳችን ነው!

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም