በጎንደር ከተማ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ነክ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

55

ጎንደር፣ ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ 18 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ነክ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ የዘማች ቤተሰቦች በማናቸውም ሁኔታ ችግር እንዳይገጥማቸውና ልጆቻቸውም ትምህርት እንዳያቋርጡ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በከተማዋ  የሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ ለዘማች ቤተሰቦች ያደረጉትን ድጋፍ ባስረከቡበት ወቅት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንዳሉት፤ ወደ ግንባር የዘመቱ የፀጥታ ሃይሎች ቤተሰቦቻቸውን በመንከባከብ አደራውን እየተወጣ ይገኛል።

ከተማ አስተዳደሩም የዘማች ቤተሰቦች ችግር እንዳያጋጥማቸው በትኩት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም ህዝቡን በማስተባባር የምግብ፣ አልባሳት፣ የመጠለያና የስራ እድል የማማቻቸት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የከተማውን ልማት ለማፋጠን እያደረጉት ካለው አስተዋጽኦ ባሻገር ለህልውና ዘመቻው መሳካት የዘማች ቤተሰቦችን በመደገፍ እያደረጉት ላለው ወገናዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የድርጅቶቹ ተወካይ አቶ ንጉሴ አለሙ በበኩላቸው፤ ለዘማች ቤተሰቦች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የዘማች ቤተሰቦችም በሰጡት አስተያየት የአገር ህልውናን ለማስጠበቅ በዘመቱ ቤተሰቦቻቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳዳሩ ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሚገኝም አረጋግጠዋል። 

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም