የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ “አብቹ አባ ቢያ” የሚል የገዳ የጀግንነት ስያሜ ሰጠ

205

አዳማ፣ ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በግንባር ተሰልፈው ሰራዊቱን በመምራት ላስመዘገቡት ድል “አብቹ አባ ቢያ” የሚል የገዳ የጀግንነት ስያሜ መስጠቱን አስታወቀ።

ህብረቱ ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ህብረት የፈጠረ ማንኛውም አካል የኦሮሞ ጠላት እንደሆነም ወስኗል።

ህብረቱ ዛሬ ባካሄደው ጉባዔ በከረዩ አባ ገዳ ላይ ጠላት የፈፀመውን ግድያ በጽኑ አውግዟል።

የህብረቱ ፀሐፊና የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ እንዳሉት፤ የኦሮሞ ህዝብ እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም ከሌሎች ወንድም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ለሀገር አንድነት የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው።

“ጠላት ‘ሀገር ፈረሰች’ ብሎ ሲጠብቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር ሰራዊቱን በአካል ተገኝተው በመምራት ህዝብን ከስጋት ከማላቀቅ ባለፈ የሀገሪቷን ህልውና ያረጋገጠ ድል እንዲመዘገብ አድርገዋል” ብለዋል ።

የመጫ ኦሮሞ አባ ገዳ እና የህብረቱ አባል አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የተመዘገበው ድል የመላው ኢትዮጵያዊያን ድል መሆኑን አመልክተዋል።

“ድሉ የውስጥና የውጭ ጠላት በሀገራችን ላይ የሸረቡትን ሴራ የበጣጠሰ ከመሆኑም ባለፈ የተጀመረውን ዘመቻ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ትልቅ ወኔ የሰነቀ ነው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገርን ለማዳን ከቤተ መንግስት ወጥተው በግንባር ጦሩን በመምራት በጠላት ላይ ላስመዘገቡት ድልና ጀግንነት የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት አድናቆትና ምስጋና መቸሩን ገልጸዋል።

“ህብረቱ በኦሮሞ የጀግና ስያሜ ሞጋሳ መሰረት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘አብቹ አባ ቢያ የሚል የገዳ ስያሜ ሰጥቷል” ሲሉ ይፋ አድርገዋል።

”ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ህብረት የፈጠረው ሸኔ የኦሮሞ ጠላት ነው” ሲሉም የህብረቱን አቋም ገልጸዋል።

ከኦሮሞ ህዝብ አንድነትና ፍላጎት በተፃረረ መልኩ ከጠላት ጋር የተሰለፉ የሸኔ ታጣቂዎች እጃቸውን ለመንግስትና ለአባ ገዳዎች እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የአርፈን ቀሎ አባገዳ ሸምል አህመድ በበኩላቸው “በአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ እኩይ ሴራ ተታለው ጫካ የገቡ የኦሮሞ ልጆች ካሉ ተመልሰው ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሆን ጠላትን ማጽዳት አለባቸው” ብለዋል።

“ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ጥምረት የፈጠረ ማንኛውም አካል የኦሮሞ ጠላት ነው፤ የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት የሞተለትን ዓላማ በመዘንጋት ከጠላት ጋር ማበር ውርደት ነው” ያሉት ደግሞ የኦዳ ሮባ ሲኮ መንዶ አባገዳ አሊይ ሙሐመድ ሱሩር ናቸው።

“በከረዩ አባ ገዳ ላይ የተፈፀመው ግድያ የኦሮሞን ህዝብ ለማዋረድ ያለመ የጠላት ተግባር በመሆኑ ፍትህ እንፈልጋለን” ብለዋል።

በከረዩ አባ ገዳ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በማውገዝ፤ ወንጀሉን የፈፀሙ አካላት በአፋጣኝ ለህግ መቅረብ እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ደግሞ የቦረና አባገዳ ኩራ ጃርሶ ናቸው።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።