በጋምቤላ ክልል የቱሪዝም ሀብቶችን ለማልማት ባለሃብቶች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

66

ጋምቤላ፣ ታህሳስ 2/2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በሚደረገው ጥረት የባለሃብቶች ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።

የክልሉን የቱሪዝም ሀብት በተጠና መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገልጿል።

የክልሉ ርዕሰ  መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ  የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በጎበኙበት ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት በጋምቤላ ብሄራዊ ፓርክን ጨምሮ በክልሉ ሰፊ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስቦች ቢኖሩም በተፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ አልዋሉም።

ባለፉት 27 ዓመታት ዘርፉ ትኩረት ተነፍጎት በመቆየቱ ሀብቶቹ በሚፈለገው ደረጃ ባለመልማታቸው ክልሉ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን ተናግረዋል።

አሁን ላይ የቱሪዝም ልማት ለዜጎች የስራ እድል ፈጠራና ለሀገሪዊ ኢኮኖሚ እድገት ያለውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት መስህቦችን ከማስተዋወቅ ጀምሮ ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል ።

በመንግስት ለተጀመሩ የቱሪዝም ልማት ስራዎች ስኬታማነት ባለሃብቶች ሙዋለ ነዋያቸውን በማፍሰስ የዘርፉን ውጤታማነት ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

ባለሀብቶች የቱሪስት መስህቦችና መዳረሻዎችን በማልማት ለጎብኝዎች ምቹ በማድረግ እራሳቸውን፣ ክልሉንና ሀገሪቱን እንዲጠቅሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ኡቦንግ ኡቻላ በበኩላቸው በክልሉ ያሉ ሰፊ የቱሪዝም መስቦች በተፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ ያልዋሉት በመሰረተ ልማት ችግርና በግንዛቤ እጥረት መሆኑን ተናግረዋል።

ቢሮው በክልሉ ያለውን የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ችግሮችን በተጠና መልኩ ለመፍታትና ሀብቱን በስፋት ለማስተዋወቅ የሚያስችል ስራ ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የማጃንግ ዞን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ፣ የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የተመዘገበውን የማጃን የተፈጥሮ ደን ጨምሮ የቡሬ፣ ሐይቅ፣ የጀይ ፋፋቴና የሌሎች በርካታ የቱሪስት ሀብቶች መገኛ መሆኑን  የዞን አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም ማይከል  ገልጸዋል።

በማጀንግ ዞን የሚገኙ  የመስብ መዳረሻዎችን ለቱሪስቶች ምቹ ለማድረግ የመሰረተ ልማት  ችግሮችን ለመቅረፍ በእቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም