የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

96

ባህርዳር፣ ታህሳስ 2/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ በመገንባት ሥራ ለማስጀመር ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ጠየቁ።

በጦርነቱ የተፈናቀሉ ተማሪዎች የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ ማመቻቸት የትምህርት ሚኒስቴር ድርሻ መሆኑን ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ተናግረዋል።

በሽብር ቡድኑ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ መገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ጌታቸው ጀምበር በመድረኩ ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳው አሸባሪ ህወሓት በኢትዮጵያዊያን ትብብር ህልሙ ከሽፏል።

ቡድኑ በወረራ ይዞ በቆየባቸው አካባቢዎች ንጸሀን ዜጎችን ገድሏል፤ ሴቶችን ደፍሯል፤ የአካል ጉዳትና ሌሎች ሰብዓዊ ቀውሶችንም አድርሷል።

እንዲሁም የህዝብ መገልገያ የሆኑና ለዓመታት የተገነቡ የጤና፣ የትምህርት፣ የውሃ፣ የግብርናና ሌሎች ተቋማትን ከመዝረፍ በተጨማሪ አውድሞ መሄዱን ተናግረዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ዜጎች በክልሉ የሚቀረጹባቸውን ከ4 ሺህ በላይ የትምህርት ተቋማት ማውደሙንም ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

የትምህርት ተቋማቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሶ ገንብቶና ጠግኖ ሥራ ለማስጀመር በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ ከክልሉ መንግስት ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

"በህልውና ጦርነቱ የፈረሱና የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ደረጃቸውን ጠብቆ ለመገንባት በሚቻለው ሁሉ ጥረት ይደረጋል" ያሉት ደግሞ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ናቸው።

"የትምህርት ተቋማቱን በጋራ ተረባርበን መልሰን መገንባት ከቻልን አሸባሪው ህወሓት ያሰበው የጥፋት ዓላማ እንዳልተሳካና ወደ ፊትም እንደማይሳካ ማሳየት እንችላለን" ብለዋል።

ትምህርት ቤቶችን መልሶ የማቋቋምና የማብቃት ኃላፊነት የክልሉ ብቻ ሳይሆን የፌዴራል መንግስቱ ጭምር መሆኑንም ፕሮፌሰር ብርሀኑ ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የትምህርት ተቋማቱ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚያግዝ መልኩ ደረጃቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ይደረጋል።

"በጦርነቱ የተፈናቀሉ ተማሪዎች የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ ማመቻቸትና መታገል ደግሞ ቀጣይ የትምህርት ሚኒስቴር ድርሻ ይሆናል" ብለዋል።

ምሁራን በጦርነቱ የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ሂደት የጉዳት መጠኑን በማጥናት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የገለጹት ደግሞ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ ናቸው።

ባለድርሻ አካላት የወደሙ ተቋማትን ፈጥኖ በመገንባት በጋራ ሊረባረቡ እንደሚገባ ጠቅሰው "ምሁራንም ተቋማቱ በተሻለ መልኩ እንዲገነቡ ሙያዊ ዕገዛ በማድረግ የድርሻችንን እንወጣለን" ብለዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋሻው አስማሜ በበኩላቸው አሸባሪ ቡድኑ በዞኑ ወረራ ከፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉንም ትምህርት ቤቶች ማውደሙን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ነፃ በወጡ አካባቢዎች የጉዳቱን መጠን በመለየት ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ "ይህን መሰረት በማድረግ የተጎዱትን የትምህርት ተቋማት በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ ይሰራል" ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ምሁራን፣ ባለሃብቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም