በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከጋምቤላ ክልል ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰባሰበ

200

ጋምቤላ፣ ታህሳስ 2/2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ከጋምቤላ ክልል ከ5 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና በአይነት ድጋፍ መሰብሰቡ ተገለጸ።

በጋምቤላ ክልል የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች አስተባባሪ ኮሚቴ አማካኝነት ከክልሉ 14 ወረዳዎችና ከጋምቤላ ከተማ ድጋፉን ማሰባሰባቸውን ለኢዜአ የገለጹት የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግሩም ገብረእየሱስ ናቸው።

ከተሰበሰበው ድጋፍ ውስጥ 1 ሚሊዮን 200 ሺህ ብሩ በጥሬ ገንዘብና ቀሪው ደግሞ በዓይነት የተሰበሰበ መሆኑን አቶ ግሩም ተናግረዋል።

ድጋፍን ያሰበሳቡት በአማርና በአፋር ክልሎች በወራሪው የህወሓት የሽብር ቡድን የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመታደግ በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን ለመወጣት እንደሆነም  ተናግረዋል።

የተሰበሰበውን ድጋፍ ለተጎጂዎች ለማድረስ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ቦታው እንደሚንቀሳቀሱ አቶ ግሩም አስታውቀዋል።  

በጋምቤላ ክልል ከሚገኙ የአማራ ተወላጆችና ከሌሎች የአካባቢው ነዋሪ ህዝቦች ጋር በመሆን የጀመሩት ድጋፍና ደጀንነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት ደግሞ ሌላው የኮሚቴ አባል አቶ ደነቀው አቤ ናቸው።

የሽብር ቡድኑን ሀገር የማፈረስ እኩይ ተግባር ለመቀልበስ እየተካሄደ ባለው ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት ላይ ለመሳተፍ ጭምር ዝግጁ መሆናቸውን ነው አቶ ደነቀው የገለጹት።