በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት የደረሰባቸው የእምነት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ሁሉም በጋራ ሊሰራ ይገባል

75

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት የደረሰባቸው የእምነት ተቋማትን መልሶ በመገንባት ዜጎች መንፈሳዊ መጽናናትን እንዲያገኙ ሁሉም በጋራ እንዲሰራ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና የእስልምና ሃይማኖት አባቶች እንደሚሉት፤ በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች ከሚደረገው ቁሳዊ ድጋፍ በተጨማሪ መንፈሳዊ መጽናናት እንዲያገኙ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡

በዚህም በተለይ የእምነት ተቋማት በወደሙባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወገኖችን በመደገፍና የእምነት ተቋማቱ መልሰው እንዲቋቋሙ በማድረግ አባቶች ሐይማኖታዊ ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምሩቃን ማሕበር ስራ አስፈፃሚ ሊቀ ትጉሐን ቀሲስ ዘለቀ ተስፋዬ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ጠንካራ ሆነው ወደ ቀደመ ህይወታቸው እንዲመለሱ የሐይማኖት አባቶች ቅድሚያ ሰጥተው ሊደግፉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተለይም የወደሙ የሐይማኖት ተቋማትን መልሶ በማቋቋም ምእመኑ በአምልኮት ቦታዎች ዳግም ተሰባስቦ መጽናናት እንዲያገኝ ሊደረግ ይገባል ነው ያሉት።

በመሆኑም ቤተክርስቲያኑዋ በአሁኑ ወቅት  የተቃጠሉና ጉዳት የደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናትን መልሶ ለማቋቋም እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ምእመናን የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች ንብረታቸው የወደመባቸውና ቤተሶቦቻቸውን ያጡ ምእመናንን የመደገፍና የማጽናናት ስራን  ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዩች የኡለማ ምክር ቤት አባል ሼህ መሀመድ ሲራጅ በበኩላቸው የሃይማኖት አባቶች ከምዕመናኑ ጋር በጋራ በመሆኑ የተጎዱ ወገኖችና የሃይማኖት ተቋማትን በዘላቂት ለማቋቋም መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

"በዜጎቻችንና በሃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ይመለከተዋል" ያሉት ሼህ መሃመድ ሲራጅ፤ ከዚህ አኳያ ሁሉም ዜጋ "ጉዳዩ የኔ ነው" በማለት በመልሶ የማቋቋም ተግባር ላይ ሊሳተፍ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ምእመናን የተቸገሩትን መርዳት ከፈጣሪ ክብር የሚያሰጥ መሆኑን በመገንዘብ ወገኖቻቸውን ሊደግፉ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ችግር የደረሰባቸውን ወገኖች መደገፍ ሐይማኖታዊ አስተምሕሮና ግዴታ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም