ከኢትዮጵያ ለመውጣት የሚያስገድድ ተጨባጭ ስጋት የለም- የታሪክ ተመራማሪ

229


ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከኢትዮጵያ ለመውጣት የሚያስገድድ ተጨባጭ ስጋት አለመኖሩን ግሪካዊው የታሪክ ተመራማሪ ገለጹ።


ተመራማሪው አንቶኒስ ካልዴሮስ ግሪክ ሪፖርተር ከተባለው የሃገራቸው ድረ-ገጽ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳብራሩት አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ ሃገራት ኤምባሲዎች ደጋግመው በሚያወጡት ማሳሰቢያ ልክ አስፈሪ ነገር በአዲስ አበባ የለም ብለዋል።


“The Greek Presence in the Horn of Africa”,የተባለና ከመቶ አመታት በፊት ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ስለመጡ የግሪክ ተወላጆች መጽሃፍ ያሳተሙት የታሪክ ተመራማሪው ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ የታሪክ አጋጣሚ በሚከሰቱም ችግሮች ምክንያት ግሪካዊያን ጥለው ሔደው እንደማያውቁም ተናግረዋል።


ከ1880ዎቹ ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግሪካውያን በአዲስ አበባና በተለያዩ አካቢዎች በባቡር ሃዲድ ስራና በተለያዩ መስኮች ላይ ተሰማርተው መቆየታቸውን ገልጸዋል።


በአሁኑ ጊዜ 500 የሚሆኑ ግሪካውያን ህጋዊ ፓስፖርት በመያዝ በኢትዮጵያ እየኖሩ መሆኑን ያተተው ዘገባው ከዚህ ቁጥር በብዙ እጥፍ የሚበልጡ ግሪካውያንም በአዲስ አበባ በድሬዳዋና በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሰላም እየኖሩ መሆኑን ከታሪክ ተመራማሪው ሰማሁ ብሎ አስነብቧል።


በአሜሪካ የሚዘወሩት አንዳንድ የምእራባውያን ሃገራት ኤምባሲዎችና አለም አቀፍ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ዜጎቻቸውና ሰራተኞቻቸው ከኢትዮጵያ በአስቸኳይ እንዲወጡ ከመወትወት ባለፈም ማስፈራሪያና ማባበያዎችን በማቅረብ ለማስወጣት ጥረት ቢያደርጉም የውጭ ሃገራት ዜጎች ኢትዮጵያን ለቀው ሲወጡ አይታዩም።