አሜሪካዊያኑ ጥንዶች ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ጫና ቢበረታባቸውም ኑሯቸውን በሀዋሳ እንደቀጠሉ ነው

94

ታህሳስ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ጫና ቢደረግባቸውም የሀገሪቱ ሠላም አስተማማኝ በመሆኑ ኑሯቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳደረጉ በሀዋሳ ከተማ የሚኖሩ አሜሪካዊያን ጥንዶች ገለጹ።

ጥንዶቹ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት በተለይም የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆሙም ጠይቀዋል።

አሜሪካዊቷ ወይዘሮ ሪችል አየለ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከሆኑት ባለቤታቸው አርጋው አየለ ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መኖር ከጀመሩ 16 ዓመታትን አስቆጥረዋል።

ጥንዶቹ በኢትዮጵያ ያለው ሠላም አስተማማኝ በመሆኑ በሀዋሳ የሚኖሩት በትዳር ዘመናቸው ካፈሯቸው አምስት ልጆቻቸው ጋር  ነው።

አቤኔዘር የተሰኘ የህፃናት መርጃ ማዕከል አቋቁመው የጤና ችግር ያጋጠማቸውን፣ በተለያየ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡና ሌሎች ማህበራዊ ችግሮች ያለባቸውን  ህፃናትን ተንከባክቦ በማሳደግና በማስተማር በጎ ሥራ ተሰማርተዋል።

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከ100 ለሚበልጡ ህፃናት ሁሉን አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ እየተደረገ መሆኑን ወይዘሮ  ሪችል ይናገራሉ።

''ወደ ኢትዮጵያ በመጣሁ ጊዜ ጥሩ የእንግዳ አቀባበልና ፍቅር አግኝቻለሁ'' ያሉት ወይዘሮ ሪችል፤ ከኢትዮጵያዊያን በህላዊ አኗኗር ዘይቤ ጋር በመላመድ በፍቅር እየኖሩባት መሆኑን  አስረድተዋል፡፡

በአሜሪካ ኤምባሲ በኩል ከኢትዮጵያ እንዲወጡ እየተደረገባቸው ባለው ከፍተኛ ጫናና አንዳንድ ምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን ስለኢትዮጵያ በሚያሰራጩት የሀሰት ዘገባና ውንጀላ በእጅጉ ማዘናቸውንም ተናግረዋል።

በሀዋሳም ሆነ ዘመድ ወዳጆቻቸው በሚገኙባት አዲስ አበባ አስተማማኝ ሰላም ስላለ እንደቤታቸው በሚቆጥሯት ኢትዮጵያ ውስጥ መኖርን ምርጫቸው ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

''ፖለቲከኛ ባልሆንም በዚህ ወቅት የአሜሪካ መንግሥትና የአውሮፓ ሀገራት ቅድሚያ እየሰጡ ያሉት ለህወሓት እንደሆነ እረዳለሁ'' ያሉት ወይዘሮ ሪችል፣ የኢትዮጵያዊያንን ድምፅ ሊሰሙ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተለይ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እያካሄደ ካለው ኢ-ፍትሃዊ ጣልቃ ገብነት እጁን ሊያነሳ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያዊያን ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚያውቁና አሁን ሀገሪቱን እየመራ ያለው መንግሥትም በዴሞክራሲያዊ መንገድ የህዝብ ይሁንታ ያገኘ መሆኑን በማስታወስ።

የወይዘሮ ሪችል ባለቤት አቶ አርጋው አየለ በበኩላቸው፤ ከአሜሪካ ኤምባሲ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር አስጊ በመሆኑ ራሳችሁን አድኑ የሚል እጅግ የበዛ ውትወታ ቢኖርም እየኖርንባት ያለችው ኢትዮጵያ የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን እንደሚሉት አይደለችም ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የሚያስወጣን አንዳችም ምክንያት አላጋጠመንም ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ይልቁንም እዚህ በመኖራቸው ደህንነትና ምቾት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ፀረ ኢትዮጵያ የሆነ አቋም ቢይዙም፤ የአሜሪካዊያን አቋም እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል ያሉት አቶ አርጋው፤ ሁለቱ ሀገሮች ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰዋል፡፡

በአሜሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት በመንግሥታቸው ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ወዳጆችን ማብዛት ያስፈልገናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች እስካሁን ለሀሰት ፕሮፓጋንዳና “የውጡ” ውትወታ ሳይበገሩ በመቆየት ለኢትዮጵያ ገፅታ የድርሻቸውን ማበርከታቸውን ገልጸው፣ ከዚህም በላይ በውጭ የሚገኙ ወዳጆቻችንን በመጋበዝና የሠላም አምባሳደር በመሆን ሚና መጫወት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያዊያንን ይቅርታ እንደሚጠይቅና ዳግም የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት እንደሚጠናከር ተስፋ አለኝ ብለዋል።

ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ ያለው ፍቅር እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን የሚናገረው ልጃቸው አዶናይ አየለ በአንዳንድ ምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን ስለ ኢትዮጵያ የሚነገረው የተሳሳተና መሆን የሌለበት ነው ይላል።

በተለያዩ አካባቢ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር እንደሚገናኝ የሚናገረው አዶናይ፣ ኢትዮጵያዊያን ትሁት፣ ደስተኛ እንዲሁም የመፍትሔና ፍትሕ ሰዎች እንደሆኑ ይናገራል። 

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም