የአሜሪካ መንግሥት ፍላጎት ኢትዮጵያን ለመደገፍ ሳይሆን ለመቆጣጠር ነው

451

ታህሳስ 1/2014/ኢዜአ/ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የጆ ባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያን ለመደገፍ ሳይሆን ለመቆጣጠር ነው ፍላጎቱ ሲሉ አሜሪካዊው የአፍሪካ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኙ ላውረንስ ፍሪማን ተናገሩ።

የአፍሪካ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኙ ላውረንስ ፍሪማን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተገኝተው የኃያላን አገራትና የአፍሪካ ግንኙነት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም፤ በተለይም አሜሪካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አፍሪካን በተመለከተ በምታራምደው የተሳሳተ አቋም ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ውጤታማ አለመሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በቀድሞ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ሊቢያ፣ አለፍ ሲልም ማሊና ኮትዲቯርን ጨምሮ የሳህል ቀጠናው የደረሰበትን ከባድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ አንስተዋል።

ይህ ውድመት የተከሰተውም አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያኑ፤ የአፍሪካ አገራትን ለመደገፍ ሳይሆን “አገራትን መቆጣጠር” የሚል የተሳሳተ የውጭ ፖሊሲ በማራመዳቸው መሆኑን ነው የገለጹት።      

በዚህም በአንዳንድ ምዕራባውያን መንግሥታት ውስጥ “የጂኦ-ፖለቲካ” እሳቤዎች መፈጠራቸውን ጠቁመው አገራት ከትብብር ይልቅ ለከንቱ የእርስ በእርስ ውድድር ተዳርገዋል ብለዋል።

በዚህ የውደድር መንፈስ የተቃኘው የአሜሪካ የጆ ባይደን አስተዳደርም ከአሜሪካ ሕዝብ ፍላጎት ውጪ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሚመራው  የኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና ያለመስጠት ሁኔታ ውስጥ መግባቱን ነው ያስረዱት።  

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት ለሕዝቡ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መገንባት መቻሏን አሜሪካ ልታደንቀው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በተጓዳኝም ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጣበት 6ኛው ብሔራዊ ምርጫ የአሜሪካ መንግሥት እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደነበረ ነው የገለጹት።        

ይህም የአሜሪካ ሕዝብ አልያም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ፍላጎት አይደለም፤ ይልቁንም የአሜሪካ መንግሥት ውስጥ ያሉ ተደማጭነት ያላቸው ፖለቲከኞች ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሳማንታ ፓወር በኦባማ የአስተዳደር ዘመን የሊቢያን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መደገፋቸውን አንስተዋል።

አሜሪካ በሊቢያ የውስጥ ጉዳይ የገባችው የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶችን ለማረጋገጥ በሚል ምክንያት መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ተ.መ.ድ እ.አ.አ በ2005 ያወጣውን ዜጎችን “የመጠበቅ ሃላፊነት” መርህን በምክንያትነት ጠቅሰዋል ብለዋል።

በመርሁ መሰረት “አገራት ዜጎቻቸውን መጠበቅ ካቃታቸው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተ.መ.ድን ቻርተር መሰረት ባደረገ መልኩ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይችላል ይላል”  

ይህንንም አመካኝተው ሊቢያ መግባታቸውን ጠቁመው ሊቢያን ማፍረሳቸውን በቁጭት ገልጸዋል።  

አሁን በኢትዮጵያ ነገሮች ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ እንደሆኑ አስመስለው የሚናገሩትና የዘር ጭፍጨፋ አለ እያሉ የሚያሰራጩት መረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት ስላሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።

ስለሆነም ኢትዮጵያዊያኖች ይህንን በመረዳት የሀገራቸውን እውነት በተገቢው መንገድ በማሳወቅ አሜሪካ አቋሟን እንድትቀይር ማድረግ አለከባቸው ብለዋል።

ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የአፍሪካ አገራት ፍላጎታቸውን ሊያስቀጥሉላቸው ከሚችሉ አገራት ጋር ወዳጅነት በመፍጠር ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

በተለይም በአፍሪካ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከጥገኝነት የተላቀቀ አስተሳሰብ በአፍሪካ ወጣቶች አእምሮ ውስጥ እንዲበለጽግ በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።