የኦሮሚያ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ13 ነጥብ 8ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

70

ሰመራ ፤ ታህሳስ1 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር ክልል በፈጸመው ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ13ነጥብ 8ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን ያስረከቡት የኦሮሚያ ክልል የአደጋ ስራ አመራርና የልማት ተነሺዎች ኮሚሽን  ኮሚሽነር አቶ ሙስጠፋ ከድር እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ቡድን ሀገር እኔ ካልመራሁ  በሚል እብሪት ተወጥሮ ጦርነት በመክፈት በህዝብና ሀገር ላይ  ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።



በተለይም የሽብር ቡድኑ በአፋርና አማራ ክልሎች በወረራ በያዛቸው ቦታዎች ያደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት አስከፊ መሆኑን አውስተዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያ ከዳር ዳር ተነቃንቀው  የሽብር ቡድንና ከጀርባው የተሰለፉ ጠላቶችን እኩይ ዓላማ እያከሸፉ ይገኛሉ ብለዋል።

በተለይም  የሀገሪቱን ገቢና ወጪ ንግድ መስመር ለመቆጣጠር ያለ-የሌለ  ሃይሉን አሟጦ ቢሞክርም  የአፋር ህዝብ ከጀግናው መከላከያ ሰራዊቱ ጋር በመሆን መመከት እንደቻለም ጠቅሰዋል።

በዚህም የኦሮሚያ ክልል መንግስትና ህዝብ  አክብሮት እንዳላቸው ገልጸው፤ በሂደቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች  ድጋፍ እንዲውል 13 ነጥብ 8ሚሊዮን ብር የሚገመት ምግብ እህል ማመቻቸታቸውን አስታውቀዋል።

ድጋፉን የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጎልቤ ሲሌ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሃት  በሀገር ላይ የደቀነውን የህልውና አደጋ በተባባረ ከንድ እየተመከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


ጠላታችን ለሀገርና ለዜጎች ስጋት በማይሆንበት  ደረጃ ላይ ለማድረስ የተጀመረው ትግል  የሁሉም ኢትዮጵያውን ንቁ ተሳትፎ የሚጠይቅ   መሆኑን ገልጸዋል

ከዚህ አኳያ የኦሮሚያ ክልል መንግስትና ህዝብ ወቅታዊ ሀገራዊ  ጥሪን የሚመጥን ወገናዊ ምላሽ በመስጠትም ወገናዊ አጋርነታቸውን በተግባር ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል።

ድጋፉም የተፈናቀሉ ዜጎች የእለት ደራሽ እርዳታ እንዲያገኙ የሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ጥረት የሚያግዝ ይሆናል ነው ያሉት።
 
የኦሮሚያ ክልል  ቀደም ሲልም  ምግብ ነክ ድጋፎችን ማድረጉን ያስታወሱት አቶ ጎልቤ፤ ለዚህም በተጎጂዎችና በክልል መንግስት ስም ምስጋና  አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም