በአሜሪካ ሁሉም ግዛቶች የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የሚሳተፉበት ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ነው

485

ታህሳስ 1 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሜሪካ ሁሉም ግዛቶች የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የሚሳተፉበት ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ነው።

ሰልፉ የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ያልተገባ ጫና በመቃወም የሚካሄድ ሲሆን፤ ሰልፉ መነሻውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አድርጎ የአሜሪካ መንግስት መቀመጫ ወደ ሆነው ‘ካፒቶል ሂል’ መድረሻውን እንደሚያደርግ ተነግሯል።

በሰልፉ ላይ በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች እየተሳተፉ ነው።

ሰልፈኞቹ የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገውን ያልተገባ ጫና የሚቃወሙ መልዕክቶችን እንደሚያስተላልፉ ነው።

ሰልፈኞቹ አሸባሪው ሕወሓት እየፈጸማቸው ያሉ አሰቃቂ ድርጊቶች እና የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚያሰራጯቸውን ሐሰተኛ መረጃዎችን በማውገዝ ላይ ይገኛሉ።

ከአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት አንስቶ እስከ ‘ካፒቶል ሂል’ በሚደረገው የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ ለአሜሪካ ዜጎች በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከቱ መረጃዎችን የያዙ በራሪ ወረቀቶች እንደሚበተኑም ተገልጿል።

ሰልፉ በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በሰልፉ ላይ በሕልውና ማስከበር ዘመቻው ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን መቆማቸውን የሚገልጹበት እንድሆነም ተመልክቷል።

በዋሺንግተን ዲሲ የሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ “የበቃ” ወይም ‘#NoMore’ ዘመቻ አካል ሲሆን፤ ሰልፉን የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዋሺንግተን ግብረ ሃይል ከተለያዩ ተቋሞችና አገር ወዳጆች በጋራ እንዳዘጋጁት ተገልጿል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።