ሀገር ከዐይን በላይ ናት!

117

  በጣፋጩ ሰለሞን (ኢዜአ)

በደቡብ ኦሞ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ ሜፀር ከተማ በ1960ዎቹ መጨረሻ ነው ይህችን ምድር የተቀላቀሉት።

ለወላጆቻቸው የበኩር ልጅ የሆኑት አቶ ግንባሩ ጋአምሺ እስከ 8ኛ ክፍል የቀለም ትምህርታቸውን በሜፀር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

በትምህርታቸው ጎበዝና አንደኛ በመውጣት የቤተሰቦቻቸውን ስም ማስጠራት የቻሉ ጎበዝ ተማሪ ነበሩ።

የማየት ችግር ስላጋጠማቸው ትምህርታቸውን ገታ በማድረግ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ክትትል ማድረግ ጀመሩ።

"በወቅቱ ሁለቱን አይኖቼን ያጣሁ ነው የመሰለኝ" ያሉት አቶ ግንባሩ የግራ አይኔ ማየት እንደሚችል ሲነገረኝ አላመንኩም።

ህክምናዬን ከጨረስኩ ከ2 ዓመት በኋላ በድጋሚ መታየት እንዳለብኝ ተነግሮኝ ከሆስፒታል ወጣሁ!

የሸገር ጎዳናዎችንና ውብ ህንፃዎችን በአግራሞት እየተመለከትኩ ወደ ሀገሬ ተመለስኩ።

"ከእንግዲህ ብርሃኔን አጥቻለሁ የኔ ነገር አበቃለት ብሎ ተስፋ የቆረጠ ሰው ብርሃኑን መልሶ ሲያገኝ የሚሰማውን ስሜት ላንተ አልነግርህም"።

ወደ ሀገሬ ከተመለስኩ በኋላ ትምህርቴን ካቆምኩበት ለመቀጠል ሞከርኩ ነገር ግን የግራ አይኔ እየተዳከመ መጣ።

ትንሽ መሳፈሪያ ትሆነኝ ዘንድ ሳንቲም ቋጥሬ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሄጄ ለመታከም አስቤ ነበር፤ አልሞላ አለኝና ወደ ጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ብሄድም ሆስፒታሉ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንድሄድ አዘዘኝ።

እጄ ላይ ሳንቲም ባለመኖሩ መሄድ ባለመቻሌ ትንሽ ገንዝብ ለማጠራቀም በማሰብ በጂንካ ከተማ በልመና ሳንቲም አጠራቅሜ ለመሄድ ወሰንኩ።

የዛሬዋን ባለቤቴንና የልጆቼን እናት ሁኔታዬን አይታ ስላዘነችልኝ ልትረዳኝ ወስና እጆቼን ይዛ ትመራኝ ጀመር።

አጋጣሚው በፈጠረው መቀራረብ የውስጣችንን አውጥተን በመነጋገር የበለጠ አንድንግባባና እንድንቀራረብ አደረገን።

መግባባቱ ወደ ፍቅር ተለውጦ በአንድ አቆራኝቶን ዛሬ ሶስት ልጆችን ወልዶ እስከ መሳም አደረሰን።

እኔ በምፅዋት ከማገኛት ገንዘብ ላይ ለህክምናዬ ትንሽ አስቀርቼ ለእለት ጉርሳችን እሰጣታለሁ።

እርሷ ደግሞ በለስ ሲቀናት ካገኘችው የቀን ስራ ለአንዳንድ ነገሮች እናውላለን።

የጂንካ ማዘጋጃ ቤት ባደረገልን ድጋፍ የመኖሪያ ቤት አግኝተን በፍቅር ኑሮአችንን እየመራን በደስታ መኖር ጀመርን።

በሁኔታዎች አለመመቻቸት ጊዜው እየነጎደ ህክምናዬን ነገ ዛሬ እያልኩ ባለሁበት ፅልመትን ገፍፌ በሀሳብ የብረሃን ጮራ አሻግሬ የማይባትን ከጠፋው የአይኔ ብርሃን በላይ እምሳሳላትን ያለችኝን ትልቋን ተስፋ የሆነችውን ሀገሬን ለማፍረስ ጠላት እየወጋት እንደሆነ ሰማሁ። አሁን ከአይኔ ብርሃን ይልቅ የሚያስጨንቀኝ የሀገሬ ጉዳይ ሆነ።

በጣም አዝኛለሁ... ሀገሬ ከፈረሰች  እኔም ልጆቼም የሚጨልምብን ያን ጊዜ ነው!

ልጆቼ አድገው ለቁምነገር በቅተው ከልመና የሚያወጡኝ ሀገሬ ስትኖር ነው !

ሀገር ከሌለች ሁሉም ከንቱ ነው!

ግን ምን ማድረግ እችላለሁ አይኖቼ ማየት ቢችሉ ወደ ግንባር በመዝመት እፋለም ነበር።እኔ ባልዘምትም ሀገሬ አንዳትፈርስና እኔም በሰላም መኖር እንድችል የመከላከያ ሰራዊቷ እየተፋለመላት መሆኑን ሰማሁና ትንሽ መረጋጋት ቻልኩ።

ቢሆንም እኔስ እሚለው ነገር ያስጨንቀኝ ገባ። ሀብት ንብረት ቢኖረኝ ያለኝን ሁሉ ሰጥቼ ሀገሬን ማገዝ በቻልኩ ደስታዬ ድርብርብ ነበር።

ዘወትር ፈጣሪ ሀገሬን አንዲያስባት በጸሎት እየተጋሁ ሳለሁ ሁሉም በሚችለው ሁሉ ለሀገር ሰላም መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው ሰራዊት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ሰማሁ።እኔስ ምን ላድርግ እያልኩ ስቆዝም ለህክምና ትሆነኛለች ብዬ በምፅዋት ያጠራቀምኳት 500 ብር ትውስ አለችኝ።

"የሀገሬ ጠላት ተወግዶ የተስፋ ብርሃን ሲፈነጥቅላት ያን ጊዜ እኔም ብርሃኔን መልሼ አገኛለሁ ብዬ በማሰብ ከባለቤቴ ጋር አወጋንና በምጽዋት ያገኘኋትን 500 ብር ለመከላከያ ያደርሱልኝ ዘንድ ለድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስረከብኩ" ብለዋል።

"ከአይኔ ብርሃን ይልቅ ለሀገሬ ቅድሚያ የሰጠሁት ሀገር ካለች ነገ ብርሃኔን በልጆቼ ማየት እችላለሁ በሚል ተስፋ ነው "ያሉት አቶ ግንባሩ ከሌላቸው ላይ ሰጡ።

ኢትዮጵያውያን በሀገር ጉዳይ ቀልድ አያውቁም፥ ህይወታቸውን ሳይሰስቱ በመስጠት ሀገር ማቆም ሁሌም ከደም ከአጥንታቸው የተዋሃደ ነው።

“ለአመታት ብርሀኑን አጥቶ ነገ አይንህ ይበራል ሲባል የዛሬን አንዴት አድሬ” አለ እየተባለ ሲተረትለት ከሚኖረው አንጻር የአቶ ግንባሩን ወሳኔ አስቲ መዝኑት።

“የአይን ብርሃኔ ሀገሬ ናት” ብለው ነጻነቷን አስጠብቃ ለመላው አፍሪካውያን የብርሀን ቀንዲል የሆነችውን ሀገራቸውን ከአሸባሪው ህወሃት ለማዳን እየተፋለሙ ላሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ለመደገፍ ይህን አደረጉ።

የአይን ብርሀኔን አገኝበታለው ብለው ተስፋ የጣሉባትንና ጓግተው ያገኟትን 500 ብር ለሀገራቸው ሰጡ።

እኛስ ከአቶ ግንባሩ ምን እንማር ይሆን?

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም