በሲዳማ ክልል ከ57 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት እየተሰራ ነው

183

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 1/2014 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል በባህላዊና ዘመናዊ መስኖ ከ57 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ባለፈው ዓመት የበልግ ወቅት በዝናብ እጥረት  ያጋጠመውን  የምርት መቀነስ ለማካካስ ለበጋ መስኖ ልማት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን  የቢሮው ሃላፊ አቶ መስፍን ቃሬ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በክልሉ ዘንድሮ በሁለት ዙር በሚካሄደው የበጋ መስኖ ልማት እንቅስቃሴ ከ57 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታቅዷል።

ለዚህም እያንዳንዱ አርሶ አደር በልማት ስራው ላይ እንዲሳተፍ አቅጣጫ ተቀምጦ በመጀመሪያው ዙር 44 ሺህ ሄክታር መሬት በመሰኖ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በበጋ መስኖ ልማት ስራው  ለአርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከማገዝ ባለፈ ከፍተኛ ገቢ በማስገኘት ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማጎልበት የሚረዱ ሰብሎች ላይ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።

በገበያ ላይ አዋጭነት  ያላቸው አትክልት፣ቅመማ ቅመም፣ፍራፍሬ፣ጥራጥሬ እና የአገዳ ሰብሎች  እንደሚለሙ  አብራርተዋል።

በቢሮው የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ክፍሌ ሻሾ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚገኙ የውሃ አማራጮችን ለመስኖ ልማት ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመስኖ ልማት ስራው ከ250 ሺህ  በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆናቸውን አመልክተው፤ እቅዱን ለማስፈጸም ከ114 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና  ከ46 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር መሰራጨቱንም አስታውቀዋል።

በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ የጋሎ አርጊሳ ቀበሌ አርሶ አደር ኤልያስ ቦጋ በሰጡት አስተያየት፤ በበጋ ወቅት በመስኖ የማልማት ልምድ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

በዘንድሮ ዓመት የግብርና ባለሙያዎች በሰጧቸው ምክረ ሀሳብ  በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ጥቅል ጎመንና ሽንኩርት በመስኖ ለማልማት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በመስኖ  በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን የሚናገሩት ደግሞ በሸበዲኖ ወረዳ ጣራመሳ ቀበሌ አርሶ አደር ዲልኬ ዲዳሞ ናቸው።

ዘንድሮ  በአምስት  ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን ለማልማት ወደስራ መግባታቸውን ነው ያስረዱት።

የጉድጓድ ውሃ በሞተር ፓምፕ በመሳብ በዓመት ሶሰት ጊዜ ለማልማት እቅድ እንዳላቸው የተናገሩት አርሶ አደር ድልኬ፤ ከሚያገኙት ምርት የተሻለ ገቢ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ህዝብና መንግስት ሀገርን ለማዳን እየተካሄደ ባለው ትግል ሁለንተናዊ ደጋፍ ከማድረጋቸው  ባሻገር የግብርናውን ጨምሮ በሌላው የልማት ዘርፍ በመትጋት ደጀንነታቸውን በተግባር እያሳዩ ነው።