አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይችል ሲገባው ትውልድ የሚገነባባቸውን ተቋማት አውድሟል

80

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይችል ሲገባው ትውልድ የሚገነባባቸውን ተቋማት ማውደሙን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ ገለጹ።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ሶስቱም ካምፓስ በአሸባሪው ህወሃት ሙሉ ለሙሉ ዘረፋና ውድመት ተፈፅሞባቸዋልም ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት "ኢትዮጵያን ማፍረስ" ግቡ አድረጎ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች የህዝብና የግለሰብ ሃብቶችን፣ የመንግስት ተቋማትን በመዝረፍ የቀረውን አውድሟል።

የሽብር ቡድኑ በገባባቸው አካባቢዎች ሴቶችን ደፍሯል፣ የእምነት ተቋማትን የውጊያ ምሽግ በማድረግ አርክሷል፤ በማቃጠልም ውድመት አስከትሏል።

በወሎ ወረራ ፈፅሞባቸው በነበሩ አካባቢዎችም ተመሳሳይ እኩይ ተግባር የፈፀመ ሲሆን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ሶስቱንም ካምፓስ ዘርፏል፤ አወድሟል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ፤ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሃት የዩኒቨርስቲውን ደሴ፣ ኮምቦልቻና ጢጣ ካምፓስ ሙሉ ለሙሉ ዘርፎታል፤ የቀረውንም አውድሞታል።

በመሆኑም የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ጨምሮ ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የሚያስተናግደው ዩኒቨርሲቲ በአሸባሪው ሃይል እንዳልነበር ሆኗል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ህንፃዎች፣ ዘመናዊ ቤተ ሙከራዎች፣ ቤተ መጻህፍት፣ የኢንተርኔት ሰርቨር እና ሌሎችም ንብረቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።

አሸባሪው ህወሃት "ኢትዮጵያን ማፍረስ" የሚል የጥፋት እቅድ ይዞ የተንቀሳቀሰ በመሆኑ በየደረሰባቸው አካባቢዎች በተለይም የህዝብ መገለገያዎችን መዝረፍና ማውደም የተለመደ ተግባሩ አድርጎታል።

በዚህም የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአሸባሪው ሃይል ዋነኛ የጥፋት ኢላማ መሆኑን ዶክተር መንገሻ ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት የሲቪል ማህበረሰብና ተቋማትን ኢላማ በማድረግ "በዓለም የጦርነት ታሪክ ያልታየ ጭካኔ የታየበት የጦር ወንጀል ፈፅሟል" ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም