አሸባሪው ህወሓት በኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ የደንበኛ እቃ ይዘው ተከማችተው የነበሩ 251 ኮንተይነሮችን ዘርፏል

78

ታህሳስ 01/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ የደንበኛ እቃ ይዘው ተከማችተው የነበሩ 251 ኮንተይነሮችን ሙሉ ለሙሉ መዝረፉንና ማውደሙን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ።

የድርጅቱ የወደብና ተርሚናል አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ምህረተአብ ተክሉ፣ በሰጡት መግለጫ የወደቡ እቃ በአሸባሪው ህወሃት በሙሉ ዘረፋና ውድመት ተፈፅሞበታል ብለዋል።

በአራት ሔክታር መሬት ላይ የተገነባው የኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ በወቅቱ 251 የደንበኞችን እቃ የያዙ ኮንተይነሮች የነበሩት ሲሆን በአካባቢው ወረራ የፈፀመው አሸባሪ ሙሉ ለሙሉ ዘርፎታል፤ ያልቻለውን ደግሞ አውድሞታል ብለዋል።

ኮንቴይነሮቹ የኢንዳስትሪ ግብዓቶችን፣ ማሽነሪዎችን፣ ምግብና መድሃኒቶችን እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶችን የያዙ እንደነበሩም ጠቅሰዋል።

ሆኖም ሁሉም ንብረቶች በአሸባሪው ህወሃት መዘረፋቸውን አቶ ምህረተአብ ገልጸዋል።

የኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ በአመት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የሚያስገኝና ለበርካቶች የስራ እድል የፈጠረና ለአገሪቷ ትልቅ የኢኮኖሚ ፋይዳ ያለው እንደነበርም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የገቢና የወጪ እቃዎች ከሚንቀሳቀሱበት ወደቦች መካከል የኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ አንዱ እንደነበርም አንስተዋል።

አሸባሪው ህወሃት በወደቡ ላይ ያደረሰውን ውድመት በተመለከተ በቀጣይ ኮሚቴ ተዋቅሮ ዝርዝር መረጃ ይቀርባል ሲሉ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚው አረጋግጠዋል።

የኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ከሚያስተዳድራቸው 8 ደረቅ ወደቦች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም